ህዝብና ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገራዊ ምርጫው ነጻና ተአማኒ እንዲሆን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝብና ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገራዊ ምርጫው ነጻና ተአማኒ እንዲሆን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ባህር ዳር፤መጋቢት 02/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖርቲዎችና ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት የዘንድሮ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻና ተአማኒ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጠየቁ።
በሀገሪቱ አንዱን መጤ፣ሌላኛውን ቤተኛ የሚያደርጉ የአስተሳሰብና የአመለካከት ዝንፈቶችን በማረም ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን ለማረጋገጥ ታቅዶ መሰራት እንዳለበትም ዋና አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ አሳስበዋል።
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 17ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ዋና አፈ ጉባኤዋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ስልጣን ላይ መውጣትና መምራት የሚቻለው ሀገርና ህዝብ ሲኖር ነው።
ምርጫ የሰለጠነ ህዝብ በሰለጠነ አግባብ ያለምንም ግርግርና ሁከት ይመራኛል የሚለውን ፓርቲ በነጻነት መርጦ ወደ ስልጣን የሚያወጣበት የዘመናዊ ስርአት መገለጫ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብና በክልሉ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገር የማሻገር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በህግ ማስከበር ዘመቻው መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በመተባበር ሀገር ለማፍረስ የተሰለፈውን የህወሓት ጁንታ ቡድንን ዓላማ በማክሸፍ ያሳዩት ተነሳሽነትና የተገኘው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
መላው ህዝብ በሀገር ጉዳይ የነበረውን የመተባበር መንፈስ በታሪክ ዳግም ያሳየበት ክስተት መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
ህዝቡ ያሳየው ትብብር አሁንም ትንኮሳ ለሚፈጽሙ የውጭና የሀገር ውስጥ ጽንፈኛ ሃይሎች ትምህርት የሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
"በደምና በአጥንት የተሳሰሩ የትግራይና የአማራ ህዝቦች በባህልና በሃይማኖት የተቆራኙና በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ናቸው" ብለዋል።
"ሀገር አፍራሽ የሆነው የትህነግ ቡድን የፈጸመው የሁለቱን ህዝቦች የመለያየት ሴራ በተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በመምከኑ የነበረውን አኩሪ ታሪክ ለማደስ የሚያስችል ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ተቀራርበው በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከርና በመወያየት የነበረውን አኩሪ ታሪክ በማደስ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አሁንም የጁንታው ፍርስራሽና የኦነግ ሸኔ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዙትን ዓላማ ለማሳካት በየትኛውም አካባቢ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ የማጥቃት ስልት የቀጠሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ማንነቱ፣ መብቱና ጥቅሙ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በእኩል ተከብሮለት የሚኖርበት ስርዓት መገንባት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቤንሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በሚካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ወይዘሮ ወርቅሰሙ አስታውቀዋል።
ሰዎች በሰውነታቸው ተከብረውና ተከባብረው እንዲኖሩ አንዱን መጤ፣ ሌላኛውን ቤተኛ የሚያደርጉ የአስተሳሰብና የአመለካከት ዝንፈቶችን በማረም ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን ለማረጋገጥ ታቅዶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስራዎች ህዝቡን በማስተባበር በተቀናጀ አግባብ ለማከናወን የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የህዝቡን ኑሮ እየተፈታተነው በመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት ችግሩን ለማረም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካላትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሃላፊነት ያለው በመሆኑ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲታረሙ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬ የጧት ውሎው በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር የቀረበውን የአስፈጻሚ አካላት የ2013 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ሪፖርት በማዳመጥ በጥንካሬዎችና ድክመቶች ዙሪያ እየመከረ ሲሆን የቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።