የአድዋ ድል አከባበር ኢትዮጵያዊያን ለአገር አንድነት የማይደራደሩ መሆኑን ያሳዩበት ነው - የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል አከባበር ኢትዮጵያዊያን ለአገር አንድነት የማይደራደሩ መሆኑን ያሳዩበት ነው - የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት
መጋቢት 1 /2013 (ኢዜአ) "የ125ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር ኢትዮጵያዊያን በአብሮነትና በአገር አንድነት እንደማይደራደሩ ያሳዩበት ነው" ሲሉ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው ገለፁ።
የአድዋ ዘማቾች የሄዱባቸውን መንገዶች በመለየት የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል።
ወርሃ የካቲትን በሙሉ ሲከበር የቆየውን የአድዋ ድል አከባበርና ውጤት አስመልክቶ ሚኒስትሯ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዓሉ ኅብረ ብሄራዊነትን ማጠናከርን፣ አድዋን በሚገባ ማስተዋወቅንና የአድዋን የትብብርና የአንድነት እሴት ለአገር ብልፅግና መጠቀምን ዓላማ አድርጎ መከበሩን ገልፀዋል።
በዓሉ በሁሉም ክልሎች በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ገልጸው፤ በአድዋ ዘመቻ ታሪክ ለፈጸሙ ጀግኖች በየአካባቢው የተለያዩ መታሰቢያዎች መሰየማቸውን ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የአድዋን ታሪክ በሚገባ እንዲያውቅ የሚያስችሉ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ በውጭ አገሮች በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በድምቀት መከበሩን አንስተዋል።
"የበዓሉ አከባበር ወጣቶች የራሳቸውን ታረክ እንዲሰሩ መነሳሳትን የፈጠረ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሁለተኛው አድዋ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ 'እንፈፅመዋለን' የሚል መነቃቃት መፍጠሩንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የበዓሉ አከባበር በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአብሮነትና ለአገር አንድነት እንደማይደራደሩ ያሳዩበት መሆኑንም አመልክተዋል።
የበዓሉ አካባበር በጋራ የሚሰሩ ስራዎች ለውጥና ውጤት እንደሚያስገኙ ልምድ የተወሰደበት እንደሆነም ሚኒስትሯ አውስተዋል።
ዶክተር ሒሩት በዓሉ በሠላም እንዲከበር ድጋፍ ያደረጉ የጸጥታ አካላትን እንዲሁም ኀብረተሰቡን አመስግነዋል።
የአድዋ ድል በዓልን የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ የአድዋ ዘማቾች የተንቀሳቀሱባቸው መንገዶች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ ሚኒስቴሩ ቦታዎቹን ለማልማት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በበዓሉ አካባበር ወቅት ለውይይት የቀረቡ ጽሁፎችን በመቀመር ለህፃናትና ለወጣቱ ትውልድ ተደራሽ በሚሆን መልኩ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።