በስነ-ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋ ለመፍጠር የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነት አለባቸው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
በስነ-ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋ ለመፍጠር የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነት አለባቸው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
መጋቢት 1/2013 (ኢዜአ) በስነ-ምግባር የታነጸ፣ አገርና ሕዝብን የሚወድ መልካም ዜጋ ለመፍጠር የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን "ለሠላም እንሰራለን ፣ በሠላም እንኖራለን፣ ዘረኝነትን እንጸየፋለን" በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል።
በበዓሉ ላይ የታደሙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የሃይማኖት ታሪክ ያላት ጥንታዊት አገር መሆኗን ገልጸዋል።
በመጽሃፍ ቅዱስ፣ በቅዱስ ቁርዓንና በአይሁድ እምነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በተደጋጋሚ መጠቀሳቸውንና አሻራቸው በጉልህ መታየቱንም ነው የጠቀሱት።
በዓለም ከሚገኙ አገራት በተለየ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ የሃይማኖት መቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል መኖሩን ገልጸው "ይህም ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ትልቅ እሴት ነው" ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እስካሁን ሕዝቡን በመልካም እየመሩ እዚህ እንዳደረሱት ሁሉ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም አሁንም ምዕመኑን በበለጠ ሊያስተምሩ እንደሚገባ ነው ፕሬዚዳንቷ የተናገሩት።
"ይሁን እንጂ ጭካኔ፣ የሰውን ልጅ ህይወት ማጥፋት ከጊዜያት በኋላ እየቀለለ መጥቶ፤ መታየት የሌለባቸው ድርጊቶች በዓይናችን እያየን በምድራችን ላይ ተከናውነዋል" ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን በማረምና በስነ-ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የጉባዔው መኖር በአገሪቷ የነበረን ክፍተት እንደሞላም ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው "በሀገራዊ ጉዳዮች የጉባዔውን አባላት በማስተባበር የሠላምና የመከባበር አሴቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ሲሰራ ቆይቷል" ብለዋል።
ባለፉት አስርት ዓመታት የሀይማኖት ተቋማትና ተከታዮቻቸው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ረጅም ርቀት የተሄደ ቢሆንም አሁንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ መሻገር እንዳልተቻለ ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ፀሃፊው "የሃይማኖት ተቋማት በድፍረት ሲቃጠሉ፣ ቅዱሳት መጻህፍት ሲራከሱና አማኞች የአንዱ ወገን በመሆናቸው ብቻ ለጥቃት ሲጋለጡ ተመልክተናል" ብለዋል።
ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ በግልጽ በመነጋገርና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማመላከት ጉባዔው የላቀ ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲችል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ጥቅምት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በይፋ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባለፉት አስርት ዓመታት ትኩረቱን ሠላምና የመከባበር እሴት ግንባታ ላይ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱና በሃይማኖት ተከታዮች መካከል አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴት እንዲጎለብት ማድረጉ ተገልጿል።
ማኅበራዊ ቀውሶችን ለመቀነስ በተለይም በሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የመከላከል ስራ በአገር አቀፍ ደረጃ መስራቱም ተነግሯል።
በተጨማሪም በስነ ምግባር፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በመንገድ ትራፊክ አደጋና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሲሰራ መቆየቱም እንዲሁ።
በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ለጉባዔው ስኬታማ ጉዞ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች የእውቅና የምስክር ወረቀትና ስጦታ ተበርክቷል።