ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ መካከል የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ መካከል የ137 ነጥብ 35 ሚሊዮን ዶላር ወይም 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪት ያስሚን ወሀብራቢ እና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲሁኔ ተፈራርመዋል።

በኢትዮጵያ እና በአለም ባንክ መካከል በዛሬው እለት የተፈረሙት ስምምነቶች ሁለት ናቸው።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ያሥሚን ወሀብረቢ እንዳሉት የመጀመሪያው ስምምነት መንግስት የኮቪድ 19 ተጽእኖን ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ይውላል፡፡

ለዚህም በዓለም ባንክ በኩል ከዓለም አቀፍ አጋርነት ለልማት የ14 ነጥብ 85 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የሁለተኛው ስምምነትም በአጠቃላይ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚውል የ122 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዓለም ባንክ በድጋፍ የተገኘው ገንዘብ ተማሪዎችና መምህራን በኮቪድ 19 እንዳይጋለጡ የሚረዳና ደህንነታቸውን በማስጠበቅ የመማር ማስተማር ሂደቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ የሚያግዝ ነው፡፡

በተጨማሪም በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በኩል መንግስት የያዛቸውን ከፍተኛ ስራዎችን ለማስፈጸም የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኡስማኔ ዲሆኔ በበኩላቸው ድጋፉ በዓለም ባንክ በኩል በዓለም አቀፍ አጋርነት ለትምህርት በተሠኘ ማዕቀፍ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ድጋፉም የኢትዮጵያ መንግስት ኮቪድ 19 ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ከጥንቃቄ ጋር እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም