ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የህዝቧ አንድነት ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም - ታማኝ በየነ

መጋቢት 1 / 2013 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የህዝቧ አንድነት ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም" ሲል አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ገለጸ።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወታደርና ዲፕሎማት ሆነው ለአገራቸው ክብርና ጥቅም እየተጉ መሆኑንም ገልጿል።

ሁለገብ የኪነ ጥበብ ባለሙያውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ፤ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና በመንግስት መካከል የሚያራርቅ አጥር እንደነበር አስታውሷል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን በንቃት የሚከታተሉ ሲሆን መልካሙን ሲያበረታቱ ያልተገባውን ድርጊት ደግሞ እንደሚነቅፉ ገልጿል።

"ይሁንና የተለየ ሀሳብ ያላቸው እንደ ጠላት የሚቆጠሩበት ሁኔታ ቢኖርም ኢትዮጵያዊያኑ ለአገራቸው ክብርና ጥቅም ወደኋላ ብለው አያውቁም" ብሏል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላም በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በርካታ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ቢኖሩትም በአገሩ ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣን ጥቃት በጋራ ለመመከት ዝግጁነት እንዳለው አብራርቷል።

ማንኛውም ዜጋ በመንግስት መዋቅር ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን በግልጽ መተቸትና እንዲስተካከሉ በማድረግ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በመግለጽ።

በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ እንደ ወታደርና እንደ ዲፕሎማት በመሆን የአገርን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መሆኑንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አብራርቷል።

"ኢትዮጵያዊያን ምንም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም በአገር ሉዓላዊነት ላይ አንድ መሆንን ከጥንት አባቶችና እናቶች ያገኙት ልምድ ነው" በማለት ተናግሯል።

እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ገለጻ፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በተለያዩ አገሮች ያሉ ኢትዮጵያዊያን በበጎ ፈቃድ ከሚሰሩት የዲፕሎማሲ ስራ ባለፈ በመንግስት የሚመደቡ ዲፕሎማቶች በቂ ዕውቀት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።

የትኛውም አገር ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ሳይሆን ችግሩን ሊያባብስ የሚችል ነገር ይዞ የሚመጣ መሆኑን በጣልያንና በሶማሊያ ወረራ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ መረዳት በቂ ነው ይላል።

ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ አንድነትና ሉዓላዊነት ከእርሱ በላይ ማንም ሊመጣለት እንደማይችል በመረዳት በጋር መቆምና የሚቃጡበትን ጥቃት በጋራ መመከት እንዳለበት ገልጿል።

በኢትዮጵያ በግልጽ የሚታዩ ውስጣዊ ችግሮችን መንግስት ጊዜ ሳይሰጥ ሊፈታ እንደሚገባም አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተማጋች ታማኝ በየነ አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም