ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከጥላቻና ጠብ አጫሪ ንግግሮች ሊቆጠቡ ይገባል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከጥላቻና ጠብ አጫሪ ንግግሮች ሊቆጠቡ ይገባል-ምሁራን
ደሴ፣መጋቢት 01/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) በዘንድሮ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያካሂዱት የምረጡኝ ቅስቀሳ ከጥላቻና ጠብ አጫሪ ንግግሮች የፀዳ ሊሆን እንደሚገባ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡
ምሁራኑ 6ኛውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መገናኛ ብዙሃን የምርጫውን ሂደት በፍትሃዊነት ሊያስተናግዱ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ጀማል ሰይድ እንደገለጹት የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና እውነተኛ እንዲሆን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነትና ሰላም ሲሉ ተቀራርበው በመነጋገርና የሚገጥሙ ችግሮችን በሰለጠነ አግባብ በመፍታት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
"በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ከጥላቻ ንግግርና ጠብ አጫሪ ጉዳዮች መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል" ያሉት አቶ ጀማል ከምንም በላይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነትን መጠበቅ የግድ የሚላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የራሳቸውን የፖለቲካ ፍጆታ ለማስጠበቅ ብሔርና ሐይማኖት ላይ የተንጠለጠሉ ፖለቲከኞች የሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መክረዋል፡፡
"ወቅቱ ቃላትና ችግር መዛዥ የበዛበት ነው" ያሉት ምሁሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሔርን፣ ሐይማኖትንና ማንነትን ከሚነኩ ቃላቶች ተቆጥበው በሰላማዊ መንገድ ብቻ አላማና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ በማሳወቅ ሀገር ለመቀራመት ያሰፈሰፉ ጠላቶችን ማሳፈር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህር አቶ ኢብራሂም ሰይድ በበኩላቸው ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ከፖለቲካ ጥቅሙ በፊት ሀገርና ህዝብን ማስቀደም ግዴታው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
''ሀገርና ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው ፖለቲካ የሚኖረው'' ያሉት ምሁሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስሜታቸውን ገድበው ከጥላቻ ንግግርና ጠብ አጫሪ ሃሳብ መውጣት የግድ የሚላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
"የዘንድሮ ምርጫ ብዙ ተስፋዎችን የያዘ በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርዱን ህግ ጠብቀው ሃሳባቸውን በነጻነት ማራመድ ይገባቸዋል" ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃኖችም ሙያዊ ስነ ምግባርን ጠብቀው የምርጫውን ሂደት በመዘገብና ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል የአየር ስዓት በመስጠት ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በምርጫ ሂደት ቅሬታ የሚገጥማቸው ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ሀሳባቸውን መግለጻቸው አይቀሬ መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ መገናኛ ብዙሀን ከፖርቲዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን በጥንቃቄ ለማስተናገድና ለመምራት ከወዲሁ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ምርጫው ከዚህ በፊት እንደነበረው የይስሙላ እንዳይሆንና በአንጻሩ እውነተኛ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ገንቢ ታሪክ ሊያኖር ይገባል" ሲሉ ምሁሩ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል።