የህብረተሰቡን ጥያቄ በአዲስ አሰራር መመለስ ያስፈልጋል -የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

84
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየታየ ያለውን አገራዊ መነቃቃት ለመጠቀምና ወደፊት ለማራመድ የህብረተሰቡን ጥያቄ በአዲስ አሰራር መመለስ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከአገሪቷ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ። ዶክተር አብይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በአገሪቷ ተስፋ ሰጪ የሆነ የህብረተሰብ መነቃቃት ቢኖርም በፍጥነት መልስ ሊያገኙ የሚገባቸው በርካታ ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለመደውን የቀድሞ አሰራር መከተል ዋስትና እንደማይሆን ጠቁመው፤ የተለመደው አሰራር አገር መለወጥ የማያስችል መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። ችግሮቹን ለመፍታት በተሻለ ዘዴና ቅልጥፍና ስራዎችን ማከናወን መፍትሄ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ለውይይት መነሻ እንዲሆን ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ስራን ከማቀድ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በምን ያህል ጊዜና ወጪ መስራት እንደሚገባ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተጨማሪ በአገሪቷ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን ከመተግበርና ውጤታማ ከማድረግ አኳያ ችግር ያለ መሆኑን ገልፀው፤ የአሰራር ስርዓቱን ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም