ቀጥታ፡

በመዲናዋ ያሉ ቴአትር ቤቶች የህፃናት ቴአትርን አካታው ቢያሳዩ መልካም ነው ተባለ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2013/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቴአትር ቤቶች የህፃናት ቴአትርን አካተው ቢያሳዩ መልካም መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ማንያዘዋል እንደሻው ገለፀ።

“ቲሚ” የተሰኘ የህፃናት ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር ቤት መታየት መጀመሩንም አርቲስቱ ገልጿል።

አንድ ምዕተ ዓመት በሞላው ዘርፍ ውስጥ አምስት ቴአትር ቤቶች ብቻ ያሉ ሲሆን ሁሉም በአዲስ አበባ ይገኛሉ።

አራቱ ቴአትር ቤቶች የአዋቂ ቴአትሮችን ሲያቀርቡ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ደግሞ የህፃናት ቴአትሮችን ብቻ ያሳያል።

በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ቴአትር ከአዋቂዎች በተጨማሪ “ቲሚ” የተሰኘና በዓይነቱ ለየት  ያለ የህፃናት ቴአትር ማሳየት ጀምሯል። 

የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ማንያዘዋል እንደሻው እንደገለፀው ቴአትሩን ማሳየት ያስፈለገው ለህፃናት ተጨማሪ አማራጮችን ለመፍጠር ታስቦ ነው።

ብዙ ግዜ የህፃናት ቴአትሮች የሚታዩት በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በመሆኑ ሌሎች ቴአትር ቤቶች የህፃናት ቴአትርን አካትተው እንዲያሳዩ ለማነቃቃትም ነው ብሏል።

“የአዋቂዎችና የህፃናት ቴአትር ጎን ለጎን መሄድ አለበት” የሚለው ማንያዘዋል የውጭ አገር ተሞክሮዎችም ይህን እንደሚያሳዩ ገልጿል። 

ቴአትር ቤቱም ይህንን እንደግዴታ በመቁጠር “ቲሚ” የተሰኘዉ የህፃናት ቴአትርን ማሳየት ጀምሯል ነው ያለው።

ቴአትሩ በቦሪስ አፕሪሊች ተፅፎ በገድሉ አሰግደው ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ መተርጎሙንና በጌታቸው ስለሺ አማካኝነት መዘጋጀቱንም አርቲስት ማንያዘዋል ገልጿል።

ቴአትሩ ለህጻናት ሰብዓዊነትና መረዳዳትን የሚያስተምር ነው ብሏል።

በቀጣይ አገር በቀል ታሪኮች ተዘጋጅተው ለህፃናት እንደሚቀርቡም ተናግሯል።

የቴአትሩ አዘጋጅ ጌታቸው ስለሺ የቴአትሩ መጀመር የወላጆችና የልጆችን ቁርኝት እንደሚያጠብቀው ገልጾ ልጆች ስለኪነጥበብ ዕውቀት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብሏል።

ቴአትሩ የኮቪድ 19መመሪያን በተከተለና ከቴአትር ቤቱ የመያዝ አቅም አንድ አራተኛውን ብቻ በመጠቀም የሚታይ መሆኑን ገልጿል።

“ቲሚ” የተሰኘው የህፃናት ቴአትር ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ 3፡30 ጀምሮ በቲአትር ቤቱ ይታያል።

የህፃናት ቴአትር በአገራችን በ1982 ዓም የተጀመረ ሲሆን ቀዳሚው በደራሲ ገድሉ አሰግደውና ሚሊዮን ፀጋዘአብ ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው "የዝናቧ እመቤት" የሚለው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ ረዥም ግዜ ያስቆጠረ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው "የአውሬዎች መሳለቂያ ኮሜዲ" /ፋቡላ/ ቴአትር በቅርቡ 100ኛ ዓመቱን መያዙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም