እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ በአድዋ ድል ገድል ያላቸው ሴቶች መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ በአድዋ ድል ገድል ያላቸው ሴቶች መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተጠየቀ
የካቲት 9/2021 (ኢዜአ) እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጨምሮ በአድዋ ድል ስኬት ገድል ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተጠየቀ።
ሴቶች በኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ ባህላዊ እሴቶች ያላቸውን ሚና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት መጠቀም ይገባልም ተብሏል።
የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ 'አድዋ ከሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ' በሚል መድረክ በአዲስ አበባ ዛሬ አካሂዷል።
የባለድርሻ ተቋማት ተወካይ ሴቶችን ባሳተፈው መድረክ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ በተለይም በአድዋ ድል የነበረው የሴቶች ተሳትፎ ተዳሷል።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አልማው ክፍሌ የኢትዮጵያ ሴቶች ከሌላው ዓለም ሴቶች በተለየ የራሳቸው ቀለም ያላቸው፣ የአመራር ልምድ ያዳበሩ፣ የመወዳደሪያ ሥነ ልቡና ያላቸው፣ ችለው አሸንፈው ያሳዩ ናቸው ይላሉ።
ከአክሱም እስከ አድዋ በነበሩ ወታደራዊ ዘመቻዎች የሴቶች ሚና ግንባር ቀደም እንደነበር አውስተው፤ "በአድዋ ጦርነት ዘማቾች 75 በመቶ ሴቶች ነበሩ" ብለዋል።
በአድዋ ጦርነት የሴቶች በተለያዩ ሙያዎች ተመድበው ከካምፕ እስከ ጦር ሜዳ ከመመገብ እስከ ማጀገን፣ ከማከም እስከ መዋጋት ድንቅ ሚና መወጣታቸውን አንስተዋል።
በጉዞ ወቅትም የማይተካ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት ዶክተር አልማው፤ በቀን ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ድርብ ድርብርብ ሃላፊነት ይዘው መዝመታቸውን ተናግረዋል።
በጦር መሪነት ደረጃም የጦርነቱን አይቀሬነት ያወቁት የውጭ ግንኙነት ቀያሿና ከ17 ሺህ በላይ ጦር መሪዋ እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የአድዋ ሴቶች "ለወንዶችም ልብ፣ ሞራልና ወኔ አቃባዮች ነበሩ" ብለዋል።
ከሴት ፊታውራሪዎች መካከልም የሶስት ሺህ ጦር መሪ የጣይቱ እህት ወይዘሮ አዛለች ብጡል፣ የከምባታ ጦር መሪዋ ወይዘሮ ልክየለሽ በየነ፣ የፊታውራሪ ገበየሁ እህት እቴነሽ ጉርሙ፣ የሶስት ሺህ ጦር መሪዋ ወይዘሮ አበበች ጨርቆሴ፣ የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ እህት ልጅ ወይዘሮ ድርቤ ጋዲሳና ወይዘሮ አመልማል ገብሬን ለአብነት ጠቅሰዋል።
'አድዋ መልከ ብዙ ቅርሳችን ነው' ያሉት የታሪክ ተማራመሪው፣ አድዋን እንደ ትምህርት ቤት፣ ሚዛን፣ ሆስፒታል፣ መስተዋት፣ ቤተ ሙከራ፣ ዐውደ ውጊያ፣ ለውጥ፣ የድል ችቦነት መስለውታል።
ሴቶች ድሉን በማስመዘገብ የተጫወቱትን ሚና ያህል፣ ገድላቸው በታሪክ በሚገባ እንዳልተወሳ ገልጸው፣ በአግባቡ ሊዘከሩ ይገባል ብለዋል።
ዛሬም የአድዋ ድል ትውፊት ወራሽ ሴቶች ያስፈልጋሉ፤ ጣይቱን መሰል ሴቶች ኢትዮጵያ ትሻለች ሲሉም ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ሳልሳዊት ባይነሳኝ ባቀረበችው ጥናታዊ ጽሁፍ አድዋን ካለጣይቱ ብጡል፣ ካለሴቶች ተሳትፎ ማሰብ አይቻልም ብላለች።
'የማርች 8 የሴቶች ቀን ሲዘከር አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ አይሆንም'፤ የቀደመ ታሪክ ያላቸው ጦር መሪዎች፣ አዝማሪዎችና ሌሎች ሁሉም የኢትዮጵያ ባለገድል ሴቶች ሊዘከሩ ይገባል ነው ያለችው።
በመሆኑም እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ የአድዋ ድል ስኬት ባለ ትልቅ ገድል ባለቤት ሴቶች መታሰቢያ ቤተ መዘከርና ሐውልት ሊቆምላቸው እንደሚገባ አንስታለች።
ለዚህ ደግሞ ሴት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቃለች።
በሌላ በኩል በቅድመ አድዋ የሴቶች ተሳትፎ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ሴቶች በታሪክ ትልቅ ተሳትፎ እንደነበራቸው አንስተዋል።
በዚህም ከጥንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች ለሰላምና ዕርቅ እሴቶች ጉልህ ሚና አላቸው ይላሉ።
'ሴቶች ያልተሳተፉበት ዘርፍ የለም' ያሉት ዶክተር ከይረዲን፣ ከመሪነት፣ ጥበበኝነት፣ ከአገር ድንበር ጠባቂነትና የዲፕሎማሲያዊ ሚናቸውን እቴጌ ጣይቱ በምሳሌነት አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች በታሪክ 'በደፈናው በዝምታ ተጎጂዎች ተደርጎ መወሰድ ስህተት ነው' ያሉት ምሁሩ፤ ሴቶች በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ በሰላምና ግጭት አፈታት ግንባር ቀደም ተሰሚነት ነበራቸው ባይ ናቸው።
ለዚህ ማሳያም በኦሮሞ ሀደ ሲንቄ፣ በሶማሌ-ሔር፣ በሲዳማ-ያካ፣ በራያ ማህበሰብ ዱበርቲዎች፣ በስልጤ-ሴረን ባህል በማሳያነት አቅርበዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው ሴቶች በአገር ግንባታ የነበራቸው ሚና ከጥንት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የቀደምት እናቶች ትውፊት ነው ብለዋል።
'የሴት ልጅ መሻሻል የአገር መሻሻል ነው' ያሉት ሚኒስትሯ፣ ሴቷ ልዩ እንክብካቤና ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላት ይገባል፣ ሴቷም የቀደምት እናትና አባቶችን የአልበገር ባይነት ትውፊት ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሴቶች ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የፖለቲካ ምስቅልቅል ለማውጣትና ኢትዮጵያን ለመበተን የሚሰሩ ኃይሎችን የማረቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በድምቀት መከበሩን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ወደፊትም ታሪክን በመዘከር አገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባውም መንግሥት የአድዋ ድል በዓልን በድምቀት እንዲዘከር ያደረገው ታሪክን ባለማወቅ ያለውን ችግር በመረዳቱ እንደሆነ አመልክተዋል።
'በታሪክ ሽኩቻ እውነተኛ ታሪካችን መንኳሰስ አይገባውም' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ወደፊትም የገለልተኛ የታሪክ ተመራማሪዎች ጥናትን መሰረት በማድረግ ታሪክን መዘከር፣ በኪነ ጥበብም ማውሳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ባለገድል ሴቶች መዘከራቸው፤ ለአሁኑ ትውልድ ሞራል እንደሚፈጥር
ገልጸው፣ ባለታሪኮችን በኪነ ጥበብ መዘከር ላይ በስፋት እንዲሰራበት ጠይቀዋል።
እንደ እቴጌ ጣይቱና መሰል እንስቶች ታሪክ ተጠንቶ ሊዘከር፣ ቀጣዩ ትውልድ እንዲያወሳቸውም መታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል ብለዋል።