ቀጥታ፡

በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ትምባሆ ማጨስን የሚከለክለው አዋጅ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2013/ኢዜአ/ በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ትምባሆ በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ ቅጣት የሚጥለው አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ገለፀ።

በመዝናኛና በሌሎች የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች የትምባሆ ምርቶችን በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ የገንዘብና የእስራት ቅጣት የሚጥለው አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የአዋጁን አፈጻጸም በሚመለከትም ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል።

በመድረኩ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በዚህ ወቅት በዓለም ላይ በየዓመቱ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በትምባሆ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያም 17 ሺህ ዜጎች ትንባሆ በሚያስከትለው ጉዳት በየዓመቱ ህይወታቸው ያልፋል።

6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ አጫሽ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያንም በትንባሆ ጭስ ምክንያት ጤናቸው ላይ ተጽዕኖ እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም በዓመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ገልፀው፤ ትንባሆ ላይ የግንዛቤ ስራ በመሰራት ብቻ ይህን ወጪ በግማሽ መቀነስ እንደሚቻል ነው ያስረዱት።

ይሁንና ትምባሆ በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ ቅጣት የሚጥለው ሕግ በትክክል እየተተገበረ አለመሆኑ ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል ይላሉ።

ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ የግንዛቤ ፈጠራ ውስንነት፣ እንዲሁም በክልል ደረጃ የተጠናከረ አደረጃጀትና መዋቅር አለመኖር አዋጁን በትክክል ተፈጻሚ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በአዋጁ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ማድረግና መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአዋጁ በትክክል ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ዶክተር ሊያ ያሳሰቡት።

ጉዳዩ ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ከማፍራት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥር 2011 ዓ.ም. ባፀደቀው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 የትምባሆ ምርቶች አጠቃቀም የሚያደርሰውን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ ግዴታዎችና ክልከላዎች ማስቀመጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም