ቀጥታ፡

የሴቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት ይሰራል- አቶ አገኘው ተሻገር

ባህር ዳር የካቲት 30/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ በማረጋገጥ የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ታሪክ የተሟላ የሚሆነው ሴቶች ለሰሩትንና ወደ ፊትም ለሚሰሯቸው ስራዎች እውቅናና ክብር መስጠት ሲቻል መሆኑ ተመልክቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ትግል የሚጠይቅ ስራ ይቀራል።

"ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ቆራጥ አቋም አለመኖርና እራሳቸው ሴቶች አዳዲስ ወጣት አመራሮችን ወደ ፊት እንዲመጡ አለመፈለግ ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል።

"እንደ ክልል የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል" ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ ነባር አመራር ሴቶችም ወጣት ሴቶች ወደ መሪነት እንዲመጡ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ሴቶች የሚመሯቸው ተቋማት በአግባቡና በብቃት እየተመሩ እንደሆነ ጠቁመው የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ መሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዘንድሮ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በፓርላማ ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎ 40 በመቶና ከዛ በላይ ለማድረግ እጩዎችን የማቅረብ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።

"የሴቶች ቀን ሲከበር ባለፈ ችግር በመቆዘም ሳይሆን የወደፊት እጣ ፈንታችንን በማሰብና በማለም ሊሆን ይገባል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው።

የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከኢትዮጵያ እድገት ጋር ተሳስሮ መተግበር እንደሚገባው ጠቁመው "ሀገርን የሚወድና የሚያከብር ሁሉ ለሴቶች ክብርና እውቅና ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ገናና ታሪክ ውስጥ የሴቶች አሻራ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ናቸው።

በዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት በነበረው የሀገር ግንባታ ሂደት ሴቶች የተጫወቱት ሚናና ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም የከፈሉት መስዋትነት በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

"ይሁንና ስርአቶቹ በተቀያየሩ ቁጥርና በነበረው የተዛባ አመለካከት ለሴቶች የተሰጠው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ትኩረት በእጅጉ የሳሳ ነበር " ሲሉ ጠቅሰዋል።

ከነበሩት ሥርአቶች ስልታዊ ጫና ከማሕበረሰቡ የአስተሳሰብ ሥርአት ጋር ተቀናጅቶ  ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዳይታዩ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።

አሁን ላይ መንግስት ለሴቶች በሰጠው ትኩረትና አጽዕኖት በተፈጠሩ መዋቅራዊ ምላሾች ትርጉም ያለው ውጤት እየታየ መሆኑን አመልክተዋል።

"የአመለካከት ችግሩ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ሊቀረፍ ባለመቻሉ ያልተሻገርናቸውና በቀጣይ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት  ልንተግብራቸው የሚገቡ በርካታ ስራዎች ይጠብቁናል'' ብለዋል።

"ሃገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች" ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህ ደግሞ ሴቶች የከፈሉት መስዋትነት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ የተሟላ የሚሆነው ሴቶች ለሰሩትና ወደ ፊትም ለሚሰሯቸው ስራዎች እውቅናና ክብር መስጠት ሲቻል በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

''የበዓሉ መከበር ዋነኛ ዓላማ ሴቶች ጥቅሞቻችንና መብቶቻችን እንዲከበሩ ተደራጅቶ መታገል እንደሚገባ ግንዛቤ መፍጠር ነው'' ያሉት ደግሞ  የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ናቸው። 

በዘርፉ የሚስተወሉ ሁለንተናዊ ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚፈቱ ባለመሆናቸው በዘላቂነት እንዲፈቱ ያልተቋረጠ ስልታዊ ትግል ይጠይቃል"።

በበዓሉ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ተወካይ ሴቶች የተገኙ ሲሆን በዓሉ በውይይት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም