ቀጥታ፡

የምርጫ አስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

የካቲት 30/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የአስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ስልጠናው የአስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ሲሆን 150 ሰልጣኞች የሚሳተፋበት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአሰልጣኞች አስተባባሪ ወይዘሪት ሰዓዳ ሃሰን እንዳሉት የስልጠናው ተሳታፊዎች መሪ ሰልጣኞች ሲሆኑ መጋቢት 4 እና 5 ቀን 2013 ዓ.ም በመላ አገሪቱ በ20 ማዕከላት ለ2 ሺህ 500 የመስክ ሰልጣኞች በተለያዩ ቋንቋዎች ስልጠና ይሰጣሉ ብለዋል።

የሰልጣኞቹ ምልመላ ከተለያዩ የሙያ ዘርፍ መከናወኑን በማስታወቅ አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የህግና የፓለቲካ ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ስልጠናው በየደረጃው ለሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ዙር ስልጠና የእጩዎች ምዝገባ ስልጠና መካሄዱን አስታውሰው ሁለተኛ ዙር ስልጠና የአስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ስልጠና መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ቀዳሚው ስልጠና ውጤታማ እንደነበር በመጠቆም ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና ውጤት ይኖረዋል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም