ቀጥታ፡

የ ''ይቀበሉ፤ይመንዝሩ ይሸለሙ'' የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማበረታቻ ዕጣ ወጣ

  አዲስ አበባ የካቲት 30/2013 የ21ኛው ዙር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ''ይቀበሉ፤ይመንዝሩ ይሸለሙ'' የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማበረታቻ ፕሮግራም የዕጣ አወጣጥ መርሃግብር ተከናወነ። ጥቁር ገበያ ለባንኮች ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

የ ''ይቀበሉ፤ይመንዝሩ ይሸለሙ'' መርሃግብር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማበረታት ፋይዳው የላቀ ነው ተብሏል።

በሽልማቱም አንድ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል፤ሁለት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ እና ሃያ ዘመናዊ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ለእድለኞች ተላልፈዋል።

በዕጣው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ50 ዶላር ጀምሮ የመነዘሩ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በባንኩ የአለም አቀፍ ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጥሩብርሃን ሃይሉ "ጥቁር ገበያ ለባንኮች ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ገንዘቡን ህጋዊ በሆነ መንገድ በመመንዘር ግለሰቦችን ከማበልጸግ በመቆጠብ አገሩን መደገፍ አለበት ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከውጭ የሚላክለትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በመመንዘር አንድም በአገሪቷ የሚካሄዱ ልማቶችን በመደገፍ የሽልማቱ ተካፋይም እንዲሆን አሳስበዋል።

ግለሰብን ማበልጸግ አገርን ለግለሰብ አሳልፎ መስጠት መሆኑን ተገንዝበው ህጋዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ አደራ ብለዋል።

መንግስትም ጥቁር ገበያውን ለማስቆም የሚወስደውን ክትትል እና እርምጃ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል ብለዋል።

ባንኩ ከሽልማቱ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚሰጡ ኤቲኤም ማሽኖችን በማዘጋጀት ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

የይመንዝሩ ይሸለሙ መርሃ ግብር ከተጀመረ በኋላ በህጋዊ መንገድ ምንዛሪ የሚፈጽሙ ግለሰቦች ቁጥር መሻሻል ማሳየቱን ወይዘሮ ጥሩብርሃን አስታውቀዋል።

ከፊታችን ካሉት የትንሳኤና የኢድአልፈጥር በአል ጋር ተያይዞ ምንዛሪ የሚያደርጉትን ለማበረታታት 22ኛ ዙር የይመንዝሩ ይቀበሉ ይሸለሙ መርሃ ግብር እንደሚቀጥል ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም