የዘንድሮ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን ሀላፊነታችንን እንወጣለን -የፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን ሀላፊነታችንን እንወጣለን -የፓርቲ አመራሮች
መተማ የካቲት 30/2013 (ኢዜአ) 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መሰረት የሚጣለበት እንዲሆን ሃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብደላ ኑሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
"ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት በሃገራዊ ጉዳዮች ተመሳሳይ አቋም ይዘን ለመስራት ከወዲሁ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረናል" ብለዋል።
ፓርቲው በምርጫው የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍታሃዊነት እንዲኖረው ከወዲሁ ለአባላትና ደጋፋፊቹ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ፓርቲውን ወክለው ለክልልና ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎችን በመምረጥ እንዲመዘገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
"ህዝቡም መብቴንና ጥቅሜን ያከብርልኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ የመምረጥ መብቱ የተረጋገጠ ነው" ብለዋል።
ህዝቡ ኢትዮጵያን የሚያሻግር፣ ውስጣዊ ሰላሟን የሚያስጠብቅና ሁለንተናዊ እድገቷን የሚያፋጥን ፓርቲን በመምረጥ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
"የዘንድሮ ምርጫ የዴሞክራሲ ፀር የሆነው የትህነግ ሃይል ከተቀበረ በኋላ የሚካሄድ መሆኑ በራሱ ምርጫው ሰላማና ፍትሃዊ እንዲሆን አንድ እድል ነው" ያለው ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ የገንዳውሃ ከተማ ማስተባበሪያ የወጣት ዘርፍ ሃላፊ ወጣት አብርሃም ሸጋው ነው።
የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው ለአባላቱና ደጋፊዎቹ ግንዛቤ መፍጠሩን ጠቁሞ "ምርጫው ህዝቡ ለሀገሪቱ እድገት ማን የተሻለ ይሰራል ብሎ በነፃነት የሚመርጥበት እንደሚሆን እምነቴ ነው" ብሏል።፡
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከስሜታዊነትና ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጩ ንግግሮች በፀዳ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።
"የዘንድሮ ምርጫ ዜጎች ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን አንድ ብለው የሚጀመሩት ይሆናል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የገንዳ ውሀ አስተባባሪ አቶ ደልዳላው አወቀ ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውንና ሃሳባቸው በነፃነት ለህዝቡና ደጋፊዎቻቸው ማድረስ የሚችሉበት አሰራር በመዘርጋት ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።