የሰመራ እና ድሬደዋ ነዋሪዎች በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሰመራ እና ድሬደዋ ነዋሪዎች በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
ሰመራ/ ድረደዋ/ደብረ ብርሀንሀምሌ 20/2010 የሰመራ እና ድሬደዋ ነዋሪዎች እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳር በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ፡፡ ከሰመራ ነዋሪዎች መካከል አቶ አህመድ አቡበከር ኢንጂነር ስመኘው በተለይ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ሂደትን በብቃት በመምራት በአባይ ወንዝ ዙሪያ ለዘመናት የነበሩ ቁጭት ምላሽ እንዲያገኝ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የሀገር ባለውለታ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ኢንጂነር ሰመኘው ለሀገራቸው ገና ብዙ መስራት የሚያስችል ሙያዊ ብቃት እያላቸው ድንገት ህይወታቸው ማለፈን ሲሰሙ ደንግጠው እንደነበር የገለጹት ደግሞ አቶ ሱለይማን ሰኢድ ናቸው፡፡ በዚህ ታላቅ ሰው ህልፈተ ህይወት ጥልቅ ሃዘን ቢሳቸውም ሰርተውት ያለፉት አኩሪ ተግባር ሁሌም በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ዘንድ ሲታወሱ እንደሚኖሩ አመልክተዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሂዳያ ጀማል ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ከራስ በላይ የሀገርን ጥቅምና እድገት በማስቀደም ያከናወናቸው ስራዎች ለኢትዮጵዊያን ምሳሌ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ከድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል መምህርት መርሻዬ ባዩ በሰጡት አስተያየት የልማት አርበኛውን የገደሉትና ሰኔ 16/2010ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የሞከሩት ጭምር በአስቸኳይ ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ "ዝምታ ሀገርና ህዝብ የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አለመሆኑን መንግስት ሊገነዘብ ይገባል" ብለዋል፡፡ ወጣት ፉአድ መሐመድ በበኩሉ እኚህን ታላቅ የሀገር ዕድገትና ብልፅግና ለማምጣት የሚሰሩ የባለሙያ የሚገድል ኢትዮጵያዊነት ያልፈጠረባቸው ጨካኞች መሆናቸውን ገልጿል፡፡ መንግስትም የሀገር ሰላም እና የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ"የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርን ትርጉም ባለው መንገድ እንዲፈታ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሌት ተቀን በበረሃ ሲሰሩ በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ " ያሉት ደግሞ አቶ መንግስቱ ይመር ናቸው፡፡ እኚን ቅን ኢትዮጵያዊ የሚገድል የሀገር ሰላምና ዕድገት የማይመኝና በመላው ሀገሪቱ ሁከት ለመፍጠር የሚራወጡ አካላት ሴራ በመሆኑ መንግስት በነዚህ ላይ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል በአማራ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ ለኢዜአ እንዳሉት ኢንጅነሩ የኢትዮጵያዊያን ተስፋ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስራን ከዳር በማድረስ የተጣለባቸውን ህዝባዊና ሀገራዊ አደራ ለመወጣት ለሰባት ዓመታት ሳይታክቱ ሰርተዋል። "በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት በቀላል የሚታይ ባለመሆኑ በዞኑ ነዋሪዎች ዘንድ ጥልቅ ሀዘን ፈጥሯል "ብለዋል። የዘመናት ቁጭት የነበረውን ብሄራዊ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ሲታገሉ በመሞታቸው ታላቅ ገድል የፈፀሙ የልማት አርበኛ እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰዋል፡፡ የጀመሩትን ልማት ከዳር ለማድረስ የዞኑ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡