ቀጥታ፡

ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ መልካም መሆኑ ተገለጸ

  አዲስ አበባ የካቲት 30/2013  ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች አያያዝ መልካም መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በመገኘት በታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

በጉብኝቱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶክተር አብረሀም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ፣ ሜጄር ጄኔራል ይርዳው ገብረመድኅን፣ ሜጄር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ፣ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር፣ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ ታሳሪዎችንም ያነጋገሩ ሲሆን ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን ኮሚሽኑ መመልከቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን መግለጻቸው እንዲሁ፡፡

የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብዓዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋ እና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው ያነሱ ታሳሪዎች አሉ ብሏል በመግለጫው፡፡

ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ ያነሱ ታሳሪዎች አሉ፡፡

አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል።

ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ የሚገኙበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ማረጋገጡን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደር ነክ ጥያቄዎች ላይ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የወንጀል ምርመራውን በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ እና የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም