ቀጥታ፡

በምርጫ ሂደቶች የሚሳተፉ ሴቶችን ከጥላቻ ንግግርና ከጾታዊ ጥቃት መከላከል ይገባል

አዲስ አበባ የካቲት 29/2013 በምርጫ ሂደቶች የሚሳተፉ ሴቶችን ከጥላቻ ንግግርና ጾታዊ ጥቃት መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስገነዘበ።

ኮሚሽኑ "መታገልን እንምረጥ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት ባስተላለፈው ጥሪ በምርጫ ሂደቶች የሚሳተፉ ሴቶችን ከጥላቻ ንግግርና ጾታዊ ጥቃት መከላከል ይገባል ብሏል።

በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት እንዲሁም በተለያየ መልኩ በምርጫው ሂደት የሚሳተፉ ሴቶች ጾታን መሰረት ላደረገ የጥላቻ ንግግርና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መከላከል አለባቸው ነው ያለው።

ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና የሴቶች መብቃት ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ዳሰሳ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ዳሰሳው በተለይም በፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና በሌሎች የምርጫ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉ ሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በፊትለፊት ለተለያዩ ጾታን መሰረት ላደረጉ የቃላትና የአካል ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ያመለክታል ሲል አስታውቋል።

በፌዴራል ደረጃ በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ላይ ያተኮረው ዳሰሳ በምርጫው ላይ በእጩነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ አስፈጻሚነት ተግባራትና በሌሎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንቅስቃሴ ያላቸው ሴቶች የተለያዩ ሥነልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው ያሳያል ብሏል በመግለጫው።

በፖለቲካና በምርጫ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩ ሴቶችን የግል ተሞክሮ እንዲሁም የፍትሕና የመንግስት አካላትን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻዎችን ልምድ ባካተተው ጥናት በተለይ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ለእነዚህ ጥቃቶች ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ለዳሰሳው ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የመኖሪያና የንግድ ቤቶቻቸውን መነጠቃቸውን፣ መታሰራቸውን፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ ከእምነት ቦታዎቻቸው መታገድን ጨምሮ በቤተሰብ እስከመገለል ድረስ ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረጉ ያስረዳሉ።

በተመሳሳይ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች ድረገጾች የፖለቲካ አቋማቸውን የሚገልጹ ሴቶችም ሆኑ በቀጥታ በምርጫው የሚሳተፉ ሴቶች በጾታቸው ላይ ላተኮሩ፣ በአካላዊ ቁመናቸው፣ በአለባበሳቸው ብሎም በማኅበራዊ ሕይወታቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ለሚያነጣጥሩ ዘለፋዎችና ሥነልቦናዊ ጉዳት ለሚያደርሱ የጥላቻ ንግግሮች ይጋለጣሉ ብሏል የኮሚሽኑ መግለጫ።

ይህን መሰል ጾታን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እንደ ጾታዊ ጥቃት የሚቆጠሩ ናቸው ሲልም አክሏል።

በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች የፍትሕና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተገለጸው ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መፍትሔ የማይሰጡና በከፊልም ራሳቸው የችግሩ አካል እንደነበሩ ታይቷል።

ይህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ተወዳዳሪዎች ከሚወክሉት ፓርቲ ወይም ከወዳጅና ዘመድ ውጭ የሚያማክሩትና የሚያበረታታቸው አካል እንዳይኖር አድርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚወክሏቸው ፓርቲዎች ራሳቸው ለዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት ቦታ አለመስጠታቸው አንዱ ችግር እንደነበረ ተገልጿል።

ይሁንና በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉና በተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የተሰማሩ ሴቶች በሙሉ፣ ሴቶች የፖለቲካ አቋማቸውን በመግለጽም ሆነ በዕጩነት ከመሳተፍ ራሳቸውን እንዳይገድቡ ይመክራሉ።

በምርጫ ወቅት በሴቶች የምርጫው ተሳታፊዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና የጥላቻ ንግግሮች ሴቶች በአንድ አገር የፖለቲካና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው በኃይል እንደማገድ ስለሚቆጠር አጠቃላይ የምርጫውን ተዓማኒነትና ፍትሐዊነት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በመሆኑም "ለምርጫ 2013 ዓ.ም ባለ ስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ" በሚል ርዕስ ኢሰመኮ ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ባዘጋጀው ሰነድ ካካተታቸው ነጥቦች አንዱ "ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ስልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የምርጫው ሂደቶች በሙሉ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ" የሚጠይቅ ነው።

በተጨማሪም የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳው "ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራትና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሁሉም የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮችና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም አይነት የኃይል እርምጃ ፈጽሞ እንዲቆጠቡ" ይጠይቃል።

"ለመታገል እንምረጥ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የ2013 ዓ.ም. ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት ኢሰመኮ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በቀጥታ የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባለ 6 ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳውን በይፋ መቀበላቸውን ቃል እንዲገቡ አስታውሷል፡፡

በተለያየ መንገድ በምርጫው ሚና የሚኖራቸው የሲቪል ማኅበረሰብና የመንግስት አካላት በተለይም በሴቶች የምርጫው ተሳታፊዎች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም ዓይነት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲከላከሉም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም