ብርሃን ለሁሉም ለማዳረስ በትኩረት እየተሰራ ነው...ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ብርሃን ለሁሉም ለማዳረስ በትኩረት እየተሰራ ነው...ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
ባህር ዳር ኢዜአ የካቲት 29/ 2013 በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽ ባልሆነባቸው የገጠርና የከተማ አካባቢዎች ''ብርሃን ለሁሉም'' በሚል ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር እንጅነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።
የበለስ ጃዊ የሃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ፕሮጀክት የምረቃ ፕሮግራም ዛሬ ተከናውኗል።
ሚኒስትሩ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በሃገሪቱ ከተለያዩ የሃይል አማራጮች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት በርካታ መዋለ ንዋይ የሃይል አማራጮችን ከውሃ፣ ንፋስ፣ እንፋሎት፣ ፀሐይ በማምረት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል።
እንዲሁም የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን፣ ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት በገጠርና በከተማ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“በሃገሪቱ በአምስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ ''ብርሃን ለሁሉም'' በሚል ፕሮግራም የኤሌክትሪክ አቅርቦትና የስርጭት ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው”ብለዋል።
በቅርብ ጊዜያትም 8 ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም 25 ፕሮጀክቶች ተጀምረው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተጠናቀው ለህዝብ ለአገልግሎት ይበቃሉ”ብለዋል።
የበለስ ጃዊ የሃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ፕሮጀክት ለበለስ ስኳር ፋብሪካ ሙሉ ሃይል እንዲያገኝ ከማስቻሉም ባለፈ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የሃይል አቅርቦት እንዲያገኙ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በየጊዜው የሃይል አቅርቦቱን በማሻሻል መሰረታዊ ችግሩን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል።
“የሃይል ማስፋፋያ ስራው የቴክኖሎጂ ሽግግር አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሃገሪቱ የህዳሴና የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን የላቀ ሚና አለው” ብለዋል።
በክልሉ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መካከለኛና ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ተስፋ የተጣለባቸው ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ሃይል እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ከተሞች ሃይል የሚፈልጉ 403 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ሃይል ማቅረብ ግዴታ መሆኑንም አስረድተዋል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል በጀመረው አግባብ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታም ርዕሰ መስተዳደሩ ጠይቀዋል።
ይህ ፕሮጀክት ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ የቀረበው ሃይል በፍጥነት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ከተሞች እንዲደርስ እንዲደረግም አሳስበዋል።
''የበለስ ጃዊ የሃይል ማስተላለፊና ማከፋፈያ ፕሮጀክት ለበለስ ስኳር ፋብሪካና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሃይል አቅርቦት የሚሰጥ ነው'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ናቸው።
መንግስት ከውሃ፣ ከፀሐይ ሃይል፣ ከንፋስ፣ ከከርሰ መድር እንፋሎት ሃይል የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ሲሆን በቀጣይ ሦስት ዓመታት አሁን ላይ ያለውን 4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ወደ 10 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የመነጨውን ሃይል በፍትሃዊነት ለማዳረስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የፌዴራልና የክልሉ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካንም ጎብኝተዋል።