ቀጥታ፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻው የሴቶች ተሳትፎ የጎላ ነበር - ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ

  አዲስ አበባ የካቲት 29/2013  በሕግ ማስከበር ዘመቻው የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንደነበር በመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ገለጹ።

ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አክብሯል።

የመከላከያ ሚኒስቴር አለም አቀፉን የሴቶች ቀን "ጀግኖቻችንን እወቋቸው አክብሯቸው!" በሚል መሪ ሃሳብ ነው ያከበረው።

በበዓሉ አከባበር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊ፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና በሕግ ማስከበር ዘመቻው የተሳተፉ የሠራዊቱ አባላት ታድመዋል።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከፍተኛ ጀብድ ለፈጸሙ ሴት የሠራዊቱ አባላት የእውቅና የምስክር ወረቀትና ስጦታም ተበርክቶላቸዋል።

የሚኒስቴሩ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ በማለፍ ራሳቸውን ከማብቃት አልፈው የኢትዮጵያን ስም በዓለም አስጠርተዋል ብለዋል።

ነገር ግን አሁንም ከማጀት ያላለፉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መኖራቸው ሃቅ ነው ብለዋል።

ሴቶች በተለያዩ የስራ መስኮች በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ እየሰሩ ቢሆንም፤ እንደ ኅብረተሰቡ ግማሽ  አካልነታቸው ግን በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።

ማኅበረሰቡ በሴቶች ብቃት ላይ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ መታረም እንዳለበትና አመራሩም ሴቶችን ለማብቃት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሠራዊቱ ከኢትዮጵያ አልፎ በተለያዩ አገራት የተሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነት እየተወጣ ባለበት ወቅት በአገር ጠባቂው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ በህወሓት ቡድን የተፈፀመውን አስነዋሪ ጥቃት ዳይሬክተሯ አስታውሰዋል።

ጀግኖች ሴት የሠራዊቱ አባላት ጥቃቱን ለመቀልበስ ያሳዩት ቆራጥነትና ልበሙሉነት አስደናቂ እንደነበረም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ እንደ ጣይቱ አይነት ጀግና ሴቶችን የምታፈራ ማህፀነ ለምለም መሆኗን ያሳየ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም ተናግረዋል።

ሴት የሠራዊቱ አባላት በሕግ ማስከበር እርምጃው ላይ አስደናቂ ገድሎችን በመፈጸም ለዘመቻው ስኬት አስተዋጽኦ እንደነበራቸውም ጠቅሰዋል።

እነዚህ ሴት የሠራዊት አባላት እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው፣ በርካታ ውጣ ውረድ አልፈው ማንኛውንም አይነት ግዳጅ መፈጸማቸው ሴቶች የማይችሉት ነገር እንደሌለ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም ብለዋል።

ይህ ወታደራዊ ጀግንነት ለሌሎች ሴቶችም ተምሳሌት እንደሚያደርጋቸው ነው ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ የገለጹት።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው አስደናቂ ገድል ለፈጸሙ ሴት የሠራዊቱ አባላት የማበረታቻ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

110ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ ዛሬ በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም