በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል አገራዊ ፈተና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል አገራዊ ፈተና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 29/2013 በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች አገራዊ ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር አስቴር ይትባረክ አገርአቀፍ ፈተናው ያለምንም የጸጥታ ችግር በተለያዩ መፈተኛ ጣቢያዎች እየተሰጠ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በክልሉ ተካሂዶ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የስነ-ልቦና ጫና ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰው ይሁንና ፈታናውን ለመውሰድ ያሳዩት ጉጉት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ፈተናውን መውሰድ ላልቻሉ ተማሪዎች ሁለተኛ ዕድል እንደሚሰጥም ነው ኢንጂነር አስቴር የገለጹት።
የትግራይ ክልል ሰሜናዊ ዞን ዋና አስተዳደር ዶክተር ቴድሮስ አረጋዊ በበኩላቸው አገርአቀፍ ፈተናውን አስመልክቶ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ለተማሪዎች ጥሪ መደረጉንና በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የሚገኙ ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።
በዚሁ መሰረት ተማሪዎቹ ዛሬ ፈተናቸውን ያለምንም ችግር መፈተን ጀምረዋል ነው ያሉት።
በዛሬው ውሎ ፈተና በተሰጠባቸው ቦታዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንደነበረ ዶክተር ቴድሮስ አረጋግጠዋል።
በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዛሬ መሰጠት የጀመረው የ12ኛ ክፍል አገርአቀፍ ፈተና እስከ መጪው ሐሙስ ይቀጥላል።