ቀጥታ፡

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎቱን ለማዘመን ጥናት እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት አሰጣጥና አመራር ሥርዓቱን ለማዘመን ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። ጥናቱ የሚካሄደው ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ከአዲስ አበባ መንገድ ትራስፖርት ባለስልጣንና ከህንድ አማካሪ ድርጅት ጋር በተደረገ ስምምነት ነው። የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ኃይሉ እንደገለጹት ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎቱን ለማዘመን ጥናት  ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ ያለው ኋላቀር አሰራር በድርጅቱ አሰራር ላይ ጫና በማሳደርና ተገልጋዩን ማርካት አለማስቻሉንም ጠቁመዋል። እንደ አቶ ልዑል ማብራሪያ የጥናቱ ውጤት በሚቀጥለው ዓመት ይፋ የሚደረግ ሲሆን ድርጅቱም ጥናቱን መሰረት በማድረግ የመፍትሄ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል። አብዛኛዎቹ የድርጅቱ አውቶቡሶች በጣም ያረጁ መሆናቸውና የሰራተኞች መልቀቅ በድርጅቱ ሥራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታትም የአውቶቡስ ጥገና በማካሄድ ላይ ሲሆን የሰራተኞች ፈልሰትን ለማስቀረት ሾፌሮችን በመቅጠርና ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር አዲስ አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ አዳዲስ አውቶቡሶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ 25ቱ ተደራራቢ አውቶቡሶች አገር ውስጥ ገብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል። እንዲሁም 100 አውቶቡሶች በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ የመኪና መገጣጠሚያ በመገጣጠም ላይ ሲሆኑ 600 የሚሆኑት ደግሞ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ላለፉት 75 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም