ቀጥታ፡

የእንሰት ምግብ አዘገጃጀትን ለማሻሻል እየተካሄደ ያለው ምርምር ተስፋ ሰጭ ነው- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አርባ ምንጭ የካቲት 29/2013 ዓ/ም /ኢዜአ/ የእንሰት ምግብ አዘገጃጀትን ለማሻሻል እየተካሄደ ያለው ምርምር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የገቢ አመራጭን ከመፍጠር አንጻር ተስፋ ሰጭ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እያካሄደ ያለውን የእንሰት ምርትና ምርታማነትና የምግብ አዘገጃጀት ምርምር ፕሮጀክት  ተመልክቷል ።

የቋሚ ኮሚቴው አባል ክቡር አቶ ናስር ካንሶ ለኢዜአ እንደገለጹት የእንሰት ሰብል ከፍተኛ የምግብነት ጥቅም ያለውና ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችል ቢሆንም በትኩረት ማጣት ተገቢውን ጥቅም እየሰጠ አይደለም ።

የተክሉን ምርትና ምርታማነት በማሻሻልም ሆነ በምግብ አዘገጃጀት ትኩረት የተሰጠው አይደለም " ያሉት አቶ ዩናስ  በተለይ የምግብ አዘገጃጀቱ ከባሀላዊ ዘዴ የተላቀቀ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ባህላዊው የእንሰት ምግብ አዘገጃጀት ሂደት እስከ ሶስት ወር የሚፈጅ፣ የጊዜና ጉልበት ብክነት ያለበትና የጥራት መጓደል የሚታትበት መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተክሉን የምግብ አዘገጃጀት ለማሻሻል እያካሄደ ባለው ምርምር ተስፋ ሰጭ ውጤት የታየበት መሆኑን አስታውቀዋል ።

የምርምር ውጤቱ የእንሰት ምግብ አዘገጃጀት ሂደቱን ወደ አስር ቀን ያሳጠረ፣ በሂደቱ የሚያጋጥመውን የምርት ብክነት በ45 በመቶ የቀነሰ  መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

"ምርምሩ በዘልማድ የሴቶች ብቻ ተደርጎ የቆየውን የእንሰት መፋቅ ስራ ወንዶች እንዲሳተፉበት ያደረገ መሆኑም ችግር ፈች ያደርገዋል" ያሉት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ፋንታዬ ቦቦሌ ናቸው።

እንሰት ከቆጮና ቡላ ባለፈ በዘመናዊ ማሽን በመታገዝ ዳቦ፣ ኩኪስ፣ ቺፕስ፣ እንጀራና ሌሎች የምግብ ዓይነቶችን ማዘጋጀት ያስቻለ የምርምር ግኝት  መፈጠሩ  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

የምርምር ውጤቱ የእንሰት ምግብ አዘገጃጀትን በማዘመን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና አማራጭ የገቢ ምንጭነት በመፍጠር እረገድ ተስፋ ሰጭ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስታውቀዋል።

በእንሰት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል እረገድ  ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በዘርፉ የመንግስት እገዛ አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቁ አመላክተዋል።

 "እንሰት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን በማገዝ አይተኬ ሚና አለው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው።

በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን  በላይ ህዝብ የእንሰት ምርት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው  የተክሉን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ምግብ አዘገጃጀት ለማሻሻል  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስትቲዩቱ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መድቦ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሶስት አመት የሚቆይ የዘርፉን የምርምር ፕሮጀክት አያካሄደ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በጋሞ ዞን  የዓባያና ጫሞ ሀይቆችንም ጎብኝተዋል።

በሀይቆቹ መጎዳት በዓሣና በቱርዝም ሀብቶች ላይ እያስከተለ ያለው ችግር በሚፈታበት ሁኔታ ላይ በተለይም ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ መሠራት በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የዞኑ አካላት ጋር መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም