ቀጥታ፡

የጾሙን ወቅት በፍቅር፣ በርህራሄ፣ በመተጋገዝና ያለው ለሌለው በማካፈል ማሳለፍ ይገባል ... ብጹዕ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2013(ኢዜአ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የዓብይ ጾምን በፍቅር፣ በርህራሄ፣ በመተጋገዝና ካለው ላይ ለሌሎች በማካፈል፤ መልካም ተግባራትን በመፈጸም እንዲያሳላፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ፡፡

ብፁዕነታቸው ዛሬ የተጀመረውን የዓብይ ጾም አስመልከተው  ጋዜጣዊ  መግለጫ  ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ዓብይ ጾም የዓለም መድሃኒት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በማድረግ የሚጾም መሆኑን ገልጸው፤ ሕዝበ ክርሰቲያኑ የጾሙን ወቅት ፈቃደ ስጋን በማዳከምና መልካም ተግባር የሆነውን ፈቃደ ነፍስ በማጎልበት ማሳለፍ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ይህን የጾም ወቅት በሠላም፣ በፍቅር፣ በመተዛዘን፣ በመተጋገዝ፣ በይቅር ባይነትና ያለው ለሌለው በማካፈል ማሳለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ወቅት መልካም ስራ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ብፁዕ አቡነ ማትያስ፤ በአገሪቷ አንዳንድ አከባቢዎች የሚታየው የሠላም መደፍረስ እንዲፈታ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡

መልካም የሆነን ስራ መስራት ከፈጣሪ ዘንድ በረከት የሚያስገኝ በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ  በጾሙ ወቅት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማገዝ ሊያሳልፍ ይገባልም ብለዋል፡፡

መንግስት የሰው ሕይወት እንዳይጎዳ፣ የእምነት ተቋማት እንዳይደፈሩና ቅርሶች እንዳይዘረፉ ለእምነት ተቋማት የሕግ ከለላ ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶችም በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ታላቅ ስፍራ ያለው የዓብይ ጾም ዛሬ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡  

በተመሳሳይ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘ-ካቶሊካዊያን የዓብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምዕመኑ በፆሙ ወቅት የታመሙትን በመጎብኘት፣ የታረዙን በማልበስ፣ የተራቡን በማብላት፣ የተጠሙን በማጠጣት፣ ያዘኑትን በማፅናናት፣ የተጣሉን በማስታረቅና በማረሚያ ቤት ያሉትን በመጠየቅ በመልካም ተግባራት እንዲያሳልፍ አሳስበዋል።

በጾም ወቅት ከሃሜትና ከቂም በቀል ፈጽሞ በመራቅ፤ "ፍቅርና ይቅርታ ሕይወታችንን እንዲገዙ መጣር አለብን" ብለዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም