የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 የህግ የበላይነት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በኢንጅነር ስመኘው በቀለ እና የብዓዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ-ህይወት ዜና እጅግ አስደንጋጭ እንደሆነ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል። "ኢንጅነር ስመኘው በህይወት ዘመኑ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ጥሎት ያለፈው ታላቅ ሙያዊ አበርክቶ በሙያ አጋሮቹ እና በትውልዱ ህሊና ውስጥ በደማቁ ታትሞ የሚዘልቅ ይሆናል" ብለዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ ሁሉም ዜጋ የጋራ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘንም ገልፀዋል። "አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ከለጋ እድሜያቸው አንስቶ ለሰላም፣ዴሞክራሲ እና ለፍትህ በጽናት የታገሉ ቆራጥ ታጋይ ነበሩ" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰማሩበት የስራ መስክም ውጤታማ የነበሩ መሆናቸውንም አውስተዋል። አገሪቱ በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ የተናገሩት አቶ ደመቀ የለውጥ እንቅስቃሴው ከዳር እንዲደርስ ጥራትና ፍጥነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ሚሊዮኖች ለለውጡ በእጅጉ መሰለፋቸውን የገለፁት አቶ ደመቀ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል አንዳንድ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች ለውጡን ለማደናቀፍ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች አሉ ብለዋል። ይሄን ድርጊት ለመቀልበስም ህብረተሰቡ ከዳር እስከ ዳር ለሰላሙ ዘብ በመቆም ጥፋት የሚፈጽሙ አካላትን ለማስተማር የህግ የበላይነት እውን እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። ለዘላቂ ለውጥ መረጋገጥ፣ ለፍቅርና ለይቅርታ ሁሉም የበኩሉን አወንታዊ ሚና መወጣት እንደሚገባም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል። "በአንዳንድ አካባቢዎች የተሰሩትን የማፍረስ፣ በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ እጅግ አሳዛኝ እና የተጀመረውን ለውጥ የማይመጥን ነው" ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ። የለውጥ እንቅስቃሴውም ከዳር እንዲደርስ የህግ የበላይነት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።