ቀጥታ፡

ለምርጫው ሰላማዊነት ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ የጋሞ አባቶች ተናገሩ

አርባ ምንጭ፤ የካቲት 29/ 2013 (ኢዜአ) ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ የጋሞ አባቶች ተናገሩ።

ምርጫውን አስመልክቶ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የጋሞ አባቶች መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ እንዳሉት   ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ  ህብረተሰቡ የበኩሉን መወጣት አለበት።

ሀገሪቱ  በአንድም በሌላ  እየተፈታተኑ ያሉ ሁኔታዎችን በመገንዘብ የሀገሬ  ጉዳይ ያገባኛል በማለት ሁሉም ለሰላም ከምንም በላይ ማሰብ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የጋሞ ህዝብ ሰላም ማስፈን የሚያስችል ባህላዊ እሴት ባለቤት ነው፤ ለዚህም እኔም ከሌሎች የጋሞ አባቶች ጋር በመሆን ለምርጫው ሰላማዊነት እሰራለሁ ብለዋል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች ጫናዎች በመፍጠር በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብቶቻችን ያጣን በመሆኑ ይህ አሁን እንዳይደገም እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አማራጮቻቸውን ብቻ በማቅረብ መወዳደር እንጂ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር በመፈጸም የህዝቡን ሰላም ከሚያደፈርሱ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች መቆጠብ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሁሉም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የጋሞ አባት ካዎ ሙልጌታ መንሳ ናቸው፡፡

ሰላም ከሌለ የህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ስለሚወድቅ እያንዳንዱ ዜጋ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከጋሞ አባቶች ጋር በመተባባር  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ አባቶች  የመሪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ካዎ ጾና አባይነህ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፀረ-ሰላም ሃይሎች በፈጠሩት ሁከት የህዝቡ ደህንነት  አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አስታውሰዋል።

የህዝቡ ሰላም ሊመለስ የቻለው መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር ባደረገው ጥረት ቢሆንም ህዝቡ ለአከባቢው ሰላም ያበረከተው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

የሀገሪቱን  ሰላም ዘላቂ እንዲሆን መንግስት የህግ የበላይነት ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

እያንዳንዱ ከራሱ፣ ቤተሰቡና ጎረቤቱ ጀምሮ ለሰላም ማሰብና የበኩሉን መወጣት እንዳለበትና እሳቸውም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሰላም በአንድ ወገን ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለሀገሪቱ ሰላም በሃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ አለባቸው  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም