ቀጥታ፡

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በስራቸው የወጣቶች አርአያ እንደሆኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ

አዲስ አበባ ሃምሌ 20/2010 ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በስራቸው የወጣቶች አርአያ እንደሆኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት የሐዘን መግለጫቸው "ኢንጂነር ስመኘው ለአገራቸው እየሰሩ ካለው ሥራ አኳያ እንኳን ሞት ጉንፋን እንዲይዛቸው አልመኝም ነበር" ብለዋል። የኢንጂነር ስመኘው ህልፈተ ህይወት ወሬ በጣም የሚያስደነግጥ፣ የሚያሳዝንና ልብ የሚነካ ቢሆንም ለአገራቸው የሰሯቸው ሥራዎች፣ ይናገሯቸው የነበሩ ቃላቶችና አስተሳሰቦች በብዙ ወጣቶች አእምሮ ውስጥ ሰርፆ ቀርቷል። የእሳቸውን ፈለግ በመከተል የጀመሯቸውንና ያልጨረሷቸውን ሥራዎች የሚጨርሱ እንዲሁም የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ ዕድገትና ህዳሴን የሚያረጋግጡ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተፈጥረዋል ብለዋል። ኢንጂነር ስመኘው የልማትና የኢትዮጵያ ኢንዱስትራላይዜሽን ጀግና እንደነበሩ የጠቆሙት ፕሬዘዳንት ሙላቱ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የዕድገት ጉዞ ብዙ ኢንጂነር ስመኘውን  የመሰሉ አገር ወዳድ ወጣቶችና ባለሙያዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል። ይህም እሳቸው የጀመሯቸውንና የሚመኙትን የኢትዮጵያ ዕድገት የሚያረጋግጡ ወጣቶችን ማፍራት አስችሏል ብለዋል። ኢንጂነር ስመኘው የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ወደ አንድ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ የሚጠበቀውንና ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ተስፋ ያሳደሩበትን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዳር ለማድረስ ሲደክሙ የነበሩ ውድ የሀገር ልጅ መሆናቸውን ገልጸዋል። የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግ ከህዝቡ የተቀበሉትን አደራ ለመወጣት ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ ሲደክሙ የነበሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነበሩ ብለዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ትላንት ማለዳ በጥይት ተመትተው በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም