በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የጸረ ተዋህሲያን መድኃኒቶች ያለህክምና ትዕዛዝ ይወሰዳሉ-የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የጸረ ተዋህሲያን መድኃኒቶች ያለህክምና ትዕዛዝ ይወሰዳሉ-የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 በኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የጸረ ተዋሲያን መድሃኒቶች ያለህክምና ትዕዛዝ እንደሚወሰዱ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ። የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር 38ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን 'መድሃኒት የተላመዱ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ስርጭታቸውን ከመከላከል አኳያ የፋርማሲ ባለሙያው ድርሻ ምንድነው?' በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ አካሂዷል። የመድሃኒቶች ከበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ጋር መላመድ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የጤና እክል ሲገጥማቸው ያለ ሃኪም ትእዛዝ ወይም በተለምዶ በሚወስዱት መድሃኒት አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው። የኢትዮጵያ ፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መስፍን ጎጂ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአለም ላይ በየአመቱ 11 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታ አምጭ ተህዋሲያን ይሞታሉ። እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ከሚከሰቱ አጠቃላይ በሽታዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት መድሃኒት በተላመዱ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚከሰቱ ናቸው ብለዋል። በዚህ ደግሞ ለመድሃኒት የማይበገሩ እስከ ሞትና የጎንዮሽ የጤና ጉዳቶች የሚያስከትሉ በሽታዎች እየተፈጠሩ ህክምናውን አዳጋች እያደረገው መጥቷልም ብለዋል። በዚህም ከምንም በላይ ታማሚዎች ለዚህ ችግር እንዳይጋለጡ የመድኃኒት ባለሙያዎች ታማሚዎች ያለህክምና ትዕዛዝ መድኃኒቶችን እንዳይወስዱ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የደርጊቱ ተባባሪ መሆን አንደሌለባቸው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በበኩላቸው የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን በሽታን ለመከላከል በጤናው ዘርፍ የተሰራው ስራ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እየሆነ አይደለም። በዚህም በማህበሩ የተዘጋጀው ጉባኤ በአገሪቱ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ከመድሃኒቶች ጋር የመላመድ ችግር በምን ሁኔታ ላይ እንዳለና በቀጣይም ምን መደረግ እንዳለበት ይዳሰስበታል ነው ያሉት። ከበሽታ አምጪ ተዋህሲያን ጋር መላመድን ለመከላከል እና ተያይዞ የሚመጣውን የጤና፣የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቅረፍም ፈዋሽነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ መድሃኒትን ለህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር በጥቂት ሰዎች ከ44 ዓመት በፊት የተቋቋመ የሙያተኞች ማህበር ሲሆን በስሩ ከ2ሺህ በላይ አባላት አሉት።