ኢዜማና አብን መጪው ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማና አብን መጪው ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታወቁ
ደሴና ደብረ ማርቆስ የካቲት 28/2013 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/ አብን/ መጪው ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገለጹ።
ፓርቲዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለደሴና ደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ደጋፊዎቻቸው ዛሬ አሰተዋውቀዋል
አዜማ በደሴ ከተማ "ብቁ ዜጋ ምቹ ሀገር" በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ፕሮግራም ላይ ምክትል ሊቀመንበሩ ዶክተር ጫኔ ከበደ እንደገለጹት ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው ሃላፊነቱን ይወጣል።
ኢትዮጵያ በብሔርና በሐይማኖት በመከፋፈል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን የሚሰሩ መኖራቸውን ጠቁመው “ኢዜማ ለመመረጥ ሲል ከውጭና ከውስጣዊ ጠላቶች ጋር አይወግንም” ብለዋል፡፡
“ለቀጣዩ ምርጫ በ406 ምርጫ ወረዳዎች ከ2 ሺህ በላይ ለክልሎችና 448 ለህዝብ ተወካዮች የሚሆኑ እጩ ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ ለአገር እንድነት፣ ሰለምና ለዜጋ ፖለቲካ ቅድሚያ በመስጠት ሃሳቡን ለህዝብ እየሸጠ የሚገኝ ፓርቲ ነው”ብለዋል።
“የውስጥና የውጪ ጠላቶች በኢትዮጵያን ጥቅም ላይ በተነሱበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተቀራርቦና ተደጋግፎ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው” ያሉት ደግሞ የፓርቲው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አስተባባሪ አቶ አማንይሁን ረዳ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን ምርጨው ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው ሁሉም ዜጋ የምርጫ ካርድ በማውጣት የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ኢዜማ አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ገብረ ስላሴ በበኩላቸው “ለወያኔ ያልጠቀመውን ህዝብን በብሔር ፖለቲካ እያባሉ ስልጣን መናፈቅን ሁሉም ፓርቲዎች ሊፀየፉት ይገባል” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ በደብረ ማርቆስ ከተማ የምርጫ ማኒፌስቶውን የማስተዋወቅ እና የምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻ ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የአብን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ መምህር መልሰው ሉሌ እንዳሉት የዛሬው የቅስቀሳ አላማ የማህብረሰቡ አብንን መደገፍ የመጨረሻ ግቡ ጠንካራ አማራን መፍጠር ነው።
በዞኑ 18 ጽህፈት ቤቶችን በመክፈት አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም በኢትዮጵያ መጻኢ እድል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“አብን የብሔር እኩልነት እንዲሰፍን፣ ህዝቦች በየትኛውም ቦታ መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበት ሁኔታ ለመፍጠር እና የችግሮች ሁሉም ምንጭ የሆነው ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል የሚሰራ ድርጅት ነው” ብለዋል።