ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ለቅዳሜና ለእሁዱ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል----የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን

መቀሌ ሀምሌ 20/2010 በትግራይ ክልል በመቀሌና በተለያዩ የዞን ከተሞች ቅዳሜና እሁድ በሚካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፍላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መኮንን ካህሳይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ህዝባዊ ሰልፎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ኃይሎች ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረጉ ናቸው። ባለፈው ወር በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተካሄደ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድርና በቅርቡ በተካሄዱ ሌሎች አገራዊና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የነበረውን የፀጥታና ሰላም የማስከበር ተሞክሮ አጠናክሮ ለመጠቀም ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስረድተዋል። በክልሉ ከፀጥታ ኃይሎች በተጨማሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ሰላምና ፀጥታ በማስከበር ሥራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በተለይ በመቀሌ ከተማ ለሚካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ በዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የክልሉ ሰንደቅ አላማዎች ተሰቅለው ከወዲሁ መውለብለብ ጀምረዋል። በክልሉ የሚካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች ዋና አላማ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን የሰላም ጥረት ለመደገፍ መሆኑን ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም