ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብን በገቢ ለመደገፍ በ21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ሱቆች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ራሱን በገቢ እንዲደግፍ በ21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ሱቆች ለምረቃ በቅተዋል።

ለምረቃ የበቁት 38 ሱቆችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 20 ተጨማሪ ክፍሎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የግዥ ሎጅስቲክስ ንብረት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ደደር በ21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ከተገነቡት ሱቆች 38ቱ የሚከራዩ፤ 20 ክፍሎች ደግሞ ለተጫዋቾችና ለዳኞች ልብስ መቀየሪያ፣ ለማስተማሪያና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ሱቆቹ ክለቡ ራሱን በራሱ ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ዕቅዶቹን ከግብ እንዲያደርስ አቅም ይሆናሉ ብለዋል። 

በቀጣይ ሱቆቹን በጨረታ በማከራየት በሚገኘው ገቢ ክለቡን የመደገፍ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ስፖርት የሚቀጭጭበት ዋነኛ ምክንያት የፋይናንስ ችግር መሆኑን አንስተዋል።

የተገነቡት ሱቆች ክለቡ ራሱን በገቢ ችሎ ዘላቂነቱን እንዲያረጋግጥ በማድረግ ፋይዳቸው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ባለው የፋይናንስ አቅምና ጎፋ አካባቢ በሚገኘው የክለቡ ቦታ ሱቆቹን መገንባቱን ገልጸው ይህም ክለቡ ወጪውን እንዲሸፍንና በስፖርቱ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

ክለቡ የተቋሙ ሠራተኞችም ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች ወጪያቸው ሙሉ ለሙሉ በመንግስት እንደሚሸፈን ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም