ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና በጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አባበ፤ የካቲት 27/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እና በቻይና በጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአንና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሁለቱ ሀገራት የጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ደህንነት ጥበቃን ለማጠናከር በአዲስ አበባ ለቡ ባቡር ጣቢያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ማምሻውን ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ሀገራት የቆየ የባህላዊ፣ የታሪካዊ እንዲሁም የስልጣኔ ግንኙነቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስክ እየተጠናከሩና እየዳበሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ቻይና በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን በማንሳት ዛሬ የተደረገዉ ስምምነትም የሁለቱን ሀገራት የቆየ አጋርነት በማጠናከር፤ በጋራ ለመልማትና ለመበልፀግ ቅድሚያ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሪፎርም እያካሄደ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ የሚመደብና ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልፀዋል።

የስምምነት ፊርማው በተካሄደበት ወቅትም የቻይና መንግስት ለባቡር ትራንስፖርቱ ደህንነት ጥበቃ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድግጓል ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ለተቋሙ የተደረገዉ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ የተደረገዉ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፊርማም ተቋሙ የሰነቀዉን ራዕይ እንዲሳካ በማድረግ የጎላ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያና በቻይናዉያን ተገንብተዉ ያለቁና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችና ወደፊትም የሚገነቡ ደህንነታቸዉ እንዲጠበቅ በማድረግ በኩልም ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሀላፊነት ወስዶ እንደሚሰራም ቃል በማግባት ለተደረገው ድጋፍም ምስጋናአቅርበዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ በኢትዮጵያ እና በቻይና የጋራ ትብብር የተሰሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ደህንነት በተጠናከረ መልኩ ለመጠበቅና የሁለትዮሽ ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የዋጋ ግምት ያላቸው በርካታ የደህንነት መሣሪያዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በድጋፍ መስጠታቸውን በአምባሳደሩ ገልፀዋል ።

ቁሳቁሶቹ ለባቡር ትራንስፖርቱ ተሳፋሪዎች የደህንነት ፍተሻ የሚያገለግሉ አምስት ኤክስሬይ የመፈተሻ መሳሪያዎች፣ ሃምሳ አምስት በእጅ የሚያዙና አምስት ተንቀሳቃሽ የብረት መፈተሻ መሳሪያዎች ሲሆኑ የባቡር መስመሩን የደህንነት ጥበቃን ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።

ቻይናዊያን እና ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ፤ ቻይናዊያን የኢትዮጵያ ትልቅ የንግድ እና የኢንቬስትመንት አጋር እንዲሁም የትላልቅ ፕሮጄክቶች ኮንትራክተር ሆና እየሰሩና የቻይና ካምፓኒዎችም ከ1600 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ አማካኝነት በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የስራ እድል እንደተፈጠረና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ሥራ ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ጥር 2018 አንስቶ ከ250 ሺህ ባላይ መንገደኞችን፣ ምግብ እና ማዳበሪያን ጨምሮ 4 ሚሊዮን ቶን ክብደት ያላቸው ሸቀጦችን ማጓጓዙንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም