ቀጥታ፡

አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከልና መዳረሻ ለማድረግ ይሰራል...ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ)  አዲስ አበባን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከልና መዳረሻ ለማድረግ ይሰራል ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በ4ኛ እና 5ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 124 የሕክምና ተማሪዎች አስመርቋል።

በምረቃ ሰነ ስርዓቱ ላይ የታደሙት ምክትል ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ የጤና ዘርፉን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እየተከናወነ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ከመላ አገሪቷ ሕክምና ፍለጋ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያን መዳረሻ እንደመሆኗ ብዙ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ነው ያሉት።

ለዚህም የሕዝቡን የሕክምና ፍላጎት የሚመጥን አቅም ለመፍጠር ሥራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።

'እስካሁንም የሆስፒታሎች የማስፋፊያ፣ የእድሳትና ግንባታቸው የተጓተቱ ጤና ተቋማትን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች ተሰርተዋል' ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አዲስ አበባ የሕክምና ቱሪዝም ማዕከልና መዳረሻ እንድትሆን ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ከተማ አስተዳደሩ የመዲናዋን የጤና ዘርፍ ለማሻሻል ጠንካራ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ግንባታቸው ሳይጀመር ከቆዩ የጤና ተቋማት መካከል የቤቴል መንዲዳና የላፍቶ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ግንባታ መጀመሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"የአበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታል" ብለዋል።

ሆስፒታሉ በሕክምና ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አየለ ተሾመ ናቸው።

ሆስፒታሉ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የአገሪቷን የጤና ስርዓት ክፍተቶች በሚሞሉ አዳዲስ የስልጠና መስኮች ጭምር በማሰልጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በበኩላቸው በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት ያለ አድልዎ ሁሉንም በእኩል ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ምሩቃኑ ዶክተር ወንድወሰን ገመቹ እና ዶክተር ኤልያስ ኃይሉ በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የዓለም ሕዝብ ስጋት የሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ለምረቃ ለበቁ ተማሪዎች ስጦታና ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም