ወጣቱ ጥሪ ሳይጠብቅ በውትድርና ሙያ በመሰልጠን አገሩን ከጠላት መጠበቅ አለበት - ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ጥሪ ሳይጠብቅ በውትድርና ሙያ በመሰልጠን አገሩን ከጠላት መጠበቅ አለበት - ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 /2013 (ኢዜአ) ወጣቱ የሚደረግለትን አገራዊ ጥሪ ሳይጠብቅ በውትድርና ሙያ በመሰልጠን አገሩን ከጠላት መጠበቅ እንደሚገባው በጡረታ ላይ የሚገኙት የቀድሞ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በዛሬው እለት ሲመርቁ "የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ወጣቶች በመከላከያና በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ በመሳተፍ የአገራችንን ህልውና የሚገዳደሩ ሃይሎች እንደማይሳካላቸው ማሳየት ይገባቸዋል” ማለታቸው ይታወቃል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ፣ "ወጣቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ደህንነት በመጠበቅ አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አገሮች ውትድርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ብሔራዊ አገልግሎት ተግባራዊ እንደሚያደርጉና ይህም ለአገራቸው እድገት አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቀሱት ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ፤ በብሔራዊ ውትድርና የሰለጠነ ሃይል ቀድሞ ማዘጋጀት አገር በጠላት የሚደርስባትን ወረራ በፍጥነት መመከት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የሰለጠነ ወታደር አገራዊ ጥሪ ሲደረግ ወደ ዘመቻ ለመግባት መሳሪያ ማስታጠቅ ብቻ የሚፈልግ በመሆኑ የግዳጅ ተልዕኮን በአግባቡ ለመፈጸም እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በሚፈለገው መጠን የሰለጠነ የወታደር ሃይል ከሌለ አገር በጠላት እንድትደፈር እንደሚያደርግ፤ ባልተዘጋጀና ባልሰለጠነ ሃይል በመዋጋት አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነት እንደሚያስከፍልም አብራርተዋል።
ስለሆነም መንግስት አገርን ከጠላት ሃይል መከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ሃይል ማዘጋጀትና አቅም ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዜጎች በውትድርና አገልግሎት ውስጥ መሳተፋቸው በስነ ምግባር የታነጹና ምርታማ ዜጋ እንደሚያደርጋቸው ገልጸው፤ ወጣቱ በውትድርና ሙያ ለማገልገል ጥሪ እስኪደረግለት መጠበቅ እንደሌለበት አመልክተዋል።
"ወጣቱ የኢትዮጵያን ደህንነትና ሉዓላዊነት ካልጠበቀ ኢትዮጵያን ማን ሊጠብቃት ነው?" ያሉት ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ፤ የውትድርና ሙያን ለመቀላቀል የሚደረግ ጥሪ ታላቅ አገርን የማገልገል እድል መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ገልጸዋል።
ውትድርና አገርና ሕዝብን በማገልግል ትልቅ ክብርና ኩራት የሚገኝበት እንደሆነና ወጣቱ በውትድርና ሙያ ማገልገልን እንደ ግዴታ ሳያየው በውትድርና በመሰልጠን ኢትዮጵያን ከወራሪ ሃይል መጠበቅ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም በቀድሞ አየር ወለድ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች በመሳተፍ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ከመንግስት፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ተቋማትና ግለሰቦች ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሠላም ሚኒስቴር የመጀመሪያ ዙር የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ስልጠና የወሰዱ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን በወዳጅነት ፓርክ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ብዙ ወጣቶች እንዲቀላቀሏቸው እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።
ከቅርብና ከሩቅ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉ ብዙ ሃይሎች ስላሉ መጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ብዙ ወጣቶች በሠራዊት ውስጥ ተቀላቅለው ከማገልገል ይልቅ በፌስቡክ እንደሚዋጉና እንደሚያዋጉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በፌስቡክ ነጻነታችንን መጠበቅ አንችልም" ነው ያሉት።
ዋጋ ከፍለን ራሳችንን ካልሰጠን በስተቀር በያላችሁበት በምትናገሩትና በምትጽፉት የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ስለማይቻል በመከላከያና በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ተሳትፈን አገራችንን መጠበቅና ህልውናዋን የሚገዳደሩ ሃይሎች የማይችሉ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል።