በደቡብ ክልል ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ
ሀዋሳ፤ የካቲት 27/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
ፍቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት ያቀረቧቸው 218 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተቀባይነት በማግኘታቸው መሆኑን ተገልጿል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አስራት አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት ፍቃዱን ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኛዎቹ በዘመናዊ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እንዲሁም በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ለመሰማራት ነው።
ለባለሀብቶቹ በገጠር 6 ሺህ 825 ሄክታር መሬት ፤ በከተማ ደግሞ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መሰጠቱን አመልክተዋል።
ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍይዳ ላላቸው ለነዚሁ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከታክስና ግንባታ መሬት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ልዩ ማበረታቻዎች መደረጉን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት ፍቃድና የግንባታ መሬት ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የምርትና አገልግሎት ሥራ ለመጀመር ወደ ሚያስችላቸው የግንባታ ሥራ መግባታቸውንና ቀሪዎቹም በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገቡ ባለሀብቶችን ከማበረታቱ በተጓዳኝ መሬት ወስደው ወደ ግንባታ የማይገቡ ባለሀብቶችን በመከታተል የእርምት እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ምርትና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ ከዚህ በፊት የኢንቨስትመንት አማራጮችን በአግባቡ ለመጠቀም ተግዳሮት የነበረውን የጸጥታ ችግር ከፀጥታ መዋቅሩ፣ባለሀብቶችና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቅርበት በመስራቱ ለውጥ መጥቷል።
በኮሚሽኑ የፖቴንሻል ጥናት ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ሙሀባ አማን በበኩላቸው በክልሉ የኢንቨስትመንት መስፋፋት እንቅስቃሴው ለአካባቢው አርሶ አደሮች የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከማመቻቸት ባለፈ የገበያ ትስስር በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል አቶአብድራዛቅ አክመል በሰጡት አስተያየት በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ ውስጥ ከ6 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ካፒታል የዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት አንድ ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ስራ ከገቡ ሁለት ወራት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በእንቅስቃሴያቸው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠማቸው ጠቅሰው ችግሩ እንዲፈታላቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው በግንባታ ሂደት ከ30 ለሚበልጡ የአካባቢ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የፋብሪካው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ ስራ ሲጀምርም ለ100 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ማቀዳቸውን ባለሀብቱ አስታውቀዋል።