ቀጥታ፡

ወላይታ ዲቻ፣ ሙገር ሲሚንቶና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ይሳተፋሉ

ወላይታ ዲቻ፣ ሙገር ሲሚንቶና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እንደሚሳተፉ ተገለጸ።

ክለቦቹ በውድድሩ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ዝግጅት መጀመራቸውም ተነግሯል።

39ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን /ሲ.ኤ.ቪ.ቢ/ አዘጋጅነት ካይሮ ላይ ከመጋቢት 22 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን ለአፍሪካ አገራት ቮሊቦል ፌዴሬሽኖች በላከው ደብዳቤ በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦችን እንዲያሳውቁ ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።  

በዚሁ መሰረት ወላይታ ዲቻ፣ ሙገር ሲሚንቶና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያን ወክለው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር መሳተፍ የሚያስላቸውን የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ ማከናወናቸውን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።

እ.አ.አ በ2020 መካሄድ የነበረበት የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መሰረዙ ይታወቃል።

ሶስቱ ክለቦች ውድድሩ ከመሰረዙ በፊት አስፈላጊውን ሂደት ጀምረው እንደነበር የገለጹት የጽህፈት ቤት ሃላፊው የተሰረዘው ውድድር ዘንድሮ እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የ2012 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመቋረጡ ቀደም ሲል የተሳትፎ ሂደቱን የመጀመሩ ክለቦች በውድድሩ እንዲሳተፉ መወሰኑን ገልፀዋል።

ክለቦቹ በውድድሩ መሳተፍ የሚያስችለውን የመጨረሻውን የምዝገባ ሂደትና ተጓዳኝ ጉዳዮች እስከ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲጨርሱ የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን የጊዜ ገደብ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሶስቱ ክለቦች የስራ ሃላፊዎች በውድድሩ እንደሚሳተፉ ገልጸው ለተሳትፎው የሚጠበቁባቸውን የወረቀት ስራዎች በማገባደድ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የወላይታ ዲቻ የቮሊቦል ክለብ አስፈላጊውን ሂደት አጠናቆ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ካይሮ ለማቅናት ዕቅድ መያዙን አስታውቋል።

ክለቦቹ ለአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ዝግጅት ማድረግ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።

ከመጋቢት 22 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር 24 ክለቦች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ወላይታ ዲቻና ሙገር ሲሚንቶ እ.አ.አ 2019 በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር በመሳተፍ በቅደም ተከተል 18ኛና 19ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቃቸው አይዘነጋም።

የአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1980 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አልሀሊ 14 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን ስድስት እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ አምስት ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም