የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር መጋቢት 12 ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር መጋቢት 12 ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም መካሄድ ይጀምራል።
ጎንደር ከተማ "በጀት የለኝም" በሚል ምክንያት በሁለተኛው ዙር ውድድር እንደማይሳተፍ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ከታህሳስ 10 እስከ የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም በባህር ዳር፣ ሃዋሳና አዲስ አበባ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል።
የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ውድድር መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም በባህር ዳር እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ እስከ መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሚቆየው ውድድር ከ11ኛ እስከ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።
"ከሚያዚያ 8 እስከ 20 ቀን 2013 ዓ.ም 14ኛ እና 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ላይ ይካሄዳሉ" ብለዋል።
የሁለት ሳምንት ጨዋታዎችን በድሬዳዋ ማካሄድ ያስፈለገው ከተማዋን የሚወክል የእጅ ኳስ ክለብ ለማቋቋምና ስፖርቱ እንዲዘወተር ንቅናቄ ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመዋል።
ከግንቦት 1 እስከ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱና የሊጉ ውድድር እንደሚጠናቀቅ ነው አቶ ሞላ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሊጉን ውድድር በሦስት ከተሞች የሚያካሂደው በስፖርቱ ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሆነና ጨዋታዎችም ያለተመልካች እየተካሄዱ መሆኑን አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበረው ጎንደር ከተማ "በጀት የለኝም" በሚል ምክንያት በሁለተኛው ዙር ውድድር እንደማይሳተፍ ማሳወቁን ፌዴሬሽኑን ገልጿል።
ጎንደር ከተማ "በውድድሩ ላይ የበጀት ችግር ስለገጠመኝ መሳተፍ አልችልም" ማለቱን የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰጠኝ አዲሱ ገልጸዋል።
"ክለቡ በውድድሩ ላለመሳተፉ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ ያልሆነና የአመራሩን ድክመት የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
ፌዴሬሽኑ ከክለቡ፣ ከከተማ አስተዳደሩና ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች መፍትሔ እንዳላመጡም ተናግረዋል።
ጎንደር ከተማ በውድድሩ ለመሳተፍ ከተለያዩ ክለቦች ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች መበተኑ ተገቢ እንዳልሆነና ክለቦች ለውድድሩ አስፈላጊውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ነው አቶ ሰጠኝ ያስረዱት።
በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ18 ነጥብ ሲመራ፤ መከላከያ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ፌዴራል ፖሊስ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘዋል።
ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ በሊጉ የመጨረሻው ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በተያያዘ ዜና የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በባህር ዳር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በባህር ዳር እስከ መጋቢት 12 ቀን በሚቆየው የውድድር መርሃ ግብር ከሰባተኛ እስከ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚካሄዱ የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ቀሪ የሁለተኛ ዙር የአራት ሳምንት መርሃ ግብሮች በሚያዚያ 2013 ዓ.ም እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የደርባ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከየካቲት 22 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው።
ይሁንና አዲሱ ተሳታፊ ክለብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የተመሰረተና የዝግጅት ጊዜ አጭር በመሆኑ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹን በተስተካካይ መርሃ ግብር እንዲያደርግ መወሰኑን ነው አቶ ተክሉ የገለጹት።
ሁለተኛው ዙር ውድድር በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ሲጀመር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውድድሩ ተካፋይ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥን ወላይታ ዲቻ በ14 ነጥብ ሲመራ፤ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ13፤ ሙገር ሲሚንቶ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ባህር ዳር ከነማ በአምስት ነጥብ በሊጉ የመጨረሻ ማለትም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።