ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ፀጋዎች ጥቅም ላይ ለማዋል የስራ ባሕል ለውጥ ያስፈልጋል - ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያን ፀጋዎች ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሕዝቡ የስራ ባሕል መለወጥ፣ ድህነትን መጠየፍና ነገን አሻግሮ የመመልከት አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሊበቃ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗ ቢነገርም በርካታ ዜጎቿ በድህነት አረንቋ ውስጥ ይገኛሉ።

ከአገሪቷ ሕዝብ 80 በመቶ የሚሆነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕይወቱን የሚመራው በግብርና ነው።

ይሁንና ግብርናውም በተበጣጠሰ መሬትና በኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ የሚሰራ በመሆኑ የዜጎችን ሕይወት በመሰረታዊነት መለወጥ አልቻለም።

ኢትዮጵያ የግብርና፣ የማዕድን፣ የቅርስና የታሪክ ፀጋዎቿን በአግባቡ ለይታ ስራ ላይ ብታውል ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደምትችል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተለይም የቱሪዝምና የማዕድን ዘርፎች እምቅ ፀጋዎች ከአምራች ኢንደስትሪው በተሻለ ገቢ ማምጣት እንደሚችሉም ነው የሚናገሩት።

የአመራርና የፖሊሲ ተመራማሪና መምህር ዶክተር አለማየሁ ደበበ ኢትዮጵያ ለግብርና ምቹ የሆነ መሬት፣  ማዕድን፣የሰው ሃብት፣የተፈጥሮና የታሪክ መስህቦች አሏት እነዚህን አልተጠቀምንም እንጂ ብለዋል።

"በሰላምና በወንድማማችነት ላይ ተመስርተን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሉንን የተፈጥሮና የታሪክ ቅርሶች  አዘምነንና መሰረተ ልማት አመቻችተን ለቱሪስት በራችንን ክፍት የምናደርግ ቢሆን ኢንደስትሪው ከሚያስገኝልን በብዙ እጥፍ የተሻለ ገቢ ልናገኝ እንችላለን።" ሲሉም ተናግረዋል።

"በዓለም አቀፍ ደረጃ  ጥሩ ስም ለማግኘት ከሰራን የማንችልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የሚያስረግጥልን የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ነው፤ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ሃብታም አገሮች አየር መንገዶች ጋር ተወዳድሮ አሸንፎ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን እጅ የማይሰጥ ተቋም መመስረት የቻልን ኢትዮጵያዊያን ያንን ታሪክ ለመድገም መስራት አለብን" ብለዋል።

"ለማደግ ርቀን ሳንሄድ ምድራችን ለማደግ የምታስችለን ናት መለወጥ ያለበት ነገር ካለ ግን የስራ ባህላችንና ስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ፤ ነገን አሻግሮ የመመልከት ድህነትን መጠየፍ ደሃ ስለሆንን መሰደድ ከድህነት አያላቅቀንም ቆም ብለን ከድህነት ጋር ግብግብ መግጠም አለብን ግብግቡ ግን በዕውቀት በጥበብ በችሎታ እና በቁርጠኝነት መሆን አለበት።" ሲሉም ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዋስይሁን በላይ "የማዕድን ሴክተሩ በደንብ የምናድግበት እንደሆነ ይሰማኛል፤ ለምሳሌ አሁን የማዕድን ሴክተሩ ብሔራዊ ባንክ ያለው የመግዣ መጠን ትንሽ ሲስተካከልና ማዕድኑን የሚያወጡ ሰዎች ያላቸው የትርፍ ተካፋይነት ሁኔታ ትንሽ ስራ ሲሰራ ለውጦች ይመጣሉ ብለዋል።

የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ፖሊሲዎችን ፕሮግራሞችን እየተዘጋጁ  የማዕድን ሴክተሩ እንዲያድግ የምናደርግ ከሆነ ከኤክስፖርት በጣም ብዙ የምናገኝበት ነው እሱ ዕድል ነው።" 

የአገሪቷን ፀጋዎች ለይቶ ስራ ላይ ለማዋል ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብና አመራር ወሳኝ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

በተለይም በከፍተኛ ወጪ የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶች ያላቸው ዘለቄታዊ ጠቀሜታና አገልግሎት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባም እንዲሁ።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መልካም ዕድሎችን ይዘው ቢመጡም ለፓርኮቹ ጥሬ ዕቃ ማቅረብ ላይ ከግንባታው ጎን ለጎን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ለአብነት ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ በየትኛውም መስክ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት አቅም እንዳላት የሚገልጹት ባለሙያዎቹ ይህን አቅም በእውቀትና በጥበብ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለእውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዕድሉን አሟጦ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህን ለማድረግ ደግሞ የስራ ባህልን ማሳደግና ድህነትን የሚጠየፍ አመለካከት መገንባት ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ቁርጠኛና ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ያለው አመራር ካገኘች በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ስራዎች መስራት እንደምትችል የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሃብቷን ለዓለም ለማስተዋወቅ የተገነቡት የገበታ ለሸገር እና ገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም