ቀጥታ፡

ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜና ትልቅ ልብ ካላቸው አገር ይገነባሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27 /2013 (ኢዜአ) “ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜና ትልቅ ልብ ካላቸው አገር ይገነባሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ወጣቶች የመከላከያና ፖሊስ ሰራዊትን ተቀላቅለው የአገር ሕልውና እንዲያስጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ሚኒስቴር የመጀመሪያ ዙር የበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት ስልጠና የወሰዱ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶችን በወዳጅነት ፓርክ በይፋ መርቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለጹት፤ አሁን ያለው ትውልድ በነጻ መስጠት ከለመደ ኢትዮጵያ ብዙዎች አረአያ የሚያደርጓት ትሆናለች።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ ምሰሶ ለመሆን ለተዘጋጁ ወጣቶች አድናቆታቸውን ገልጸው፤ “ከ100 ሚሊዮን መካከል በነጻ የተሰጣችሁን ስለሆነ ከፍ ያለ ክብር ሊሰማችሁ ይገባል” ብለዋል።

“የምንቀናባቸው ያደጉ አገሮች በነጻ የሚያገለግሉ ዜጎች አሏቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ዜጎቻቸው አገራቸውን መገንባት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የሩሲያ ምሁራን ‘ድልና ስንፍና ተጋብተው ብዙ አይቆዩም’ የሚል አባባል እንዳላቸው ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድል ማስመዝገብ የሚፈልግ ከስንፍና መራቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በነጻ ለማገልገል የተነሳሱት ወጣቶች ከስንፍና ለመራቅ ዝግጁ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸው፤ “ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜና ትልቅ ልብ ካላቸው አገር ይገነባል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም