ቀጥታ፡

አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ባላሟሉ አምራቾችና አስመጪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ( ኢዜአ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 253 አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ አሟልተው ባልተገኙ አምራቾችና አስመጪዎች በሚያቀርቧቸው የንግድ ምርቶች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገለጸ።

ሚኒስቴሩ አገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ በሚገቡ የንግድ ምርቶች ጥራት ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ምክክር ከምግብና ምግብ-ነክ፣ ከኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር እየመከረ ነው።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ለኢዜአ እንዳሉት ፋብሪካዎች ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚቀርቡ ምርቶችን ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም የጥራት ችግር እየገጠማቸው ነው።

ጥራቱን ለማስጠበቅና ለመቆጣጠርም ሚኒስቴሩ 253 አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ በማውጣት በሰው ጤንነት፣ በአገር ኢኮኖሚ እና በእንስሳትና አካባቢ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብሎ በለያቸው ምርቶች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የሚገልጹት።

ኢትዮጵያ የምርቶቹን ጥራት ለማስጠበቅ ያወጣቻቸውን አስገዳጅ የንግድ ምርት ጥራት ደረጃ አሟልተው ያልተገኙት አብዛኞቹ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች መሆናቸውን አስታውቋል።

እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ ለሰው ጤንነት ጥሩ ያልሆኑ ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ በተደረገው ቁጥጥር በቅርቡ 5 ሺህ 235 ካርቶን ዘይት ወደ አገር ውስጥ ሊገባ ሲል እንዲመለስ ተደርጓል።

ስለሆነም ምርቶቹን ከውጭ ወደ አገር የሚያስገቡ በቅድሚያ የጥራት ማረጋገጫ ማሟላት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከግብይትና ከዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘም ያለ በቂ ምክንያት ጭማሪ ባደረጉ የመጠጥ ፋብሪካዎች ላይ ማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

በምክክሩ ላይ የተገኙ የፋብሪካ ተወካዮች በበኩላቸው ፋብሪካዎቻቸው አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ አሟልተው እንዲገኙ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የንግድ ምርቶችን ጥራት ለማስጠበቅ በአምራቾችና በአቅራቢዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ የአገሪቱን አስገዳጅ የጥራት ደረጃ በማስጠበቅ ወደ ገበያ እየገቡ ያሉ ምርቶች የጥራት ችግር እንዳይኖር በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም