የካራማራ ድል ህብረ ብሔራዊና ህዝባዊነት የታየበት አኩሪ ገድል ነው- በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ የቀድሞ ጦር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የካራማራ ድል ህብረ ብሔራዊና ህዝባዊነት የታየበት አኩሪ ገድል ነው- በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ የቀድሞ ጦር አባላት
ሐረር፣ የካቲት 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) የካራማራ ድል ህብረ ብሔራዊና ህዝባዊነት የታየበት አኩሪ ገድል መሆኑን በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ የቀድሞ ጦር አባላት አስታወቁ።
"በሀገሪቱ ታሪክ ከ30 አመት በኋላ ድሉ እንዲከበር መደረጉ ዳግም እንደተወለድን ቆጥረነዋል፤ በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡም ሆነ በህይወት ያለነው የተካስንበት ነው" ሲሉ በጦርነቱ የተሳተፉ የሰራዊት አባላት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ድሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊከበር እንደሚገባም የሰራዊት አባላት ጠይቀዋል።
በወቅቱ በ20ኛው ክፍለ ጦር የእግረኛ አባል የሆኑት የሃምሳ አለቃ አለማየው ተሰማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሰራዊት አባላት መካከል አንዱ ናቸው።
የሀምሳ አለቃ አለማየሁ የካራማራን ድል ሲገልጹ "ጦርነቱ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህዝብ ተሳትፎ የተካሄደ ጦርነት ነው" ሲሉ በማስታወስ ነው።
"ጦርነቱ፣ ህዝቡና በወቅቱ የበሩት እድሮችና ማህበራት ያላቸውን ቁሳቁስ በማዋጣት፣ ወታደሩን በመመገብ፣ ቁስለኛውን በማከምና ሌሎች ተሳትፎ በማከናወን ህብረ ብሔራዊነታቸውን ያሳዩበት ነው" ሲሉ ገልጸውታል ።
በወቅቱ ሀያላን የውጭ ሀገራት በተለያየ በኩል ተጽዕኖ አድርገውብን ነበር፤ ይሁንና ከኩባና ከሌሎች አጋሮቻችን ጋር በመሆን ተጽዕኖውን ተቋቁመን የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ ም ለድል በቅተናል" ብለዋል።
የካራማራ ታሪካዊ ድልና በጦርነቱ ታሪክ የሰራን ሰራዊት የደርግ መንግስት ከተለወጠበት ከ1983 ዓም በኋላ እንደ እቃ ተወርውሮ ሲበተን በዓሉም እንዳይከበር ተደርጎ መቆየቱን አስታውሰዋል ።
የድል በዓሉ እንዲከበር በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማ ማጣታቸውን ተናግረዋል።
"አሁን ላይ ከመጣው ሀገራዊ ለውጥ ማግስት በኋላ በዓሉ መከበሩ ቢያስደስተንም በሁሉም አካባቢዎች ሊከበር ይገባል" ሲሉ ጠይቀዋል::
"የካራማራ ጦርነት ሀገራዊና ህብረ-ብሐራዊነት የታየበት ጦርነት ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የሀረር ከተማ ነዋሪና በወቅቱ ተዋጊ ወታደር የነበሩት መቶ አለቃ ወንድምአገኝ ላሽተው ናቸው።
"የካራማራ ድልን ያስገኘ ሰራዊት ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ ሀገሪቱን ለ30 ዓመታት ያስተዳድር የነበረው የወያኔ መንግስት ያደረጋችሁት ጦርነት ህጋዊ ያልሆነ ነው በሚል እንደ ጨፍጫፊ ቆጥሮ ሰራዊቱን ለችግር እንዲዳረግ አድርጎታል" ብለዋል።
የወያኔ መንግሰት ድሉ ለ30 ዓመት ስሙ እንዳይነሳ ቢያደርግም ሰራዊቱ ጠንካራ፣የተማረና ብርቱ እንዲሁም በተለያዩ አካዳሚ ተምሮ በብቃት የወጣ በመሆኑ አሁንም ለሀገር ባለውለታነቱን እንደጠበቀ ለመኖር የበቃ መሆኑን ተናግረዋል።
መቶ አለቃ ወንድምአገኝ አክለው "ሰራዊቱ እሰካሁን በሀገሪቱ ልማት ላይ በግልና በጋራ እየተሳተፈና ሀገሪቱ ለምታደርገው ጥሪ ምላሽ እየሰጠ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል" ብለዋል::
የለውጡ መንግስት የካራማራ ጦርነት ታሪክን መርምሮ የድል በዓሉ እንዲከበር ማድረጉ የወደቀን ነገር እንደማንሳት ነው፤ ለእኔ ደግሞ ዳግም እንደተወለድኩ ነው የቆጠርኩት፤ በቀጣይም በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች ሊከበር ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ በየትኛውም ሀገር ላይ ወረራ አድርጋ አታውቅም፤ በጠላቶቿ ግን በተደጋጋሚ ተወራለች ፤በዚህም ዳር ድንበሯን አስከብራለች" ያሉት ደግሞ የሀረር ከተማ ነዋሪና በወቅቱ ታንከኛ የነበሩት ሻምበል ዳኛቸው አዱ ናቸው።
"በካራማራ የተደረገው ውጊያ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘን የሚገኙ ህዝቦች የተሳተፉበትና በአጭር ጊዜ ወራሪውን ሃይል ድል በማድረግ ዳር ድንበር እንዲከበር የተደረገበት ህዝባዊ ድል ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
የለውጡ መንግስት የድል በዓሉን እንዲከበር ማድረጉ በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡ፣ አጥንታቸውን ለከሰከሱ፣ ደማቸውን ላፈሰሱና በህይወት ያለን ጀግኖች የተካስንበት ነው" ብለዋል::
"ድሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደመሆኑ ሁሉም ሊያከብረው ይገባል" ያሉት ሻምበል ዳኛቸው ወጣቱ ትውልድ ከዚህ በመማር አንድነቱን ማጠናከርና ለሀገርና ዳር ድንበር መታገል እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል::
የሶማሊያ ጦር በምስራቅ በኩል 700 ኪሜ.፣በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሜ. የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ ወረራ የፈጸመበት ጦርነት የኢትዮጵያ ሰራዊት ባጭር ጎዜ ወራሪውን ጠራርጎ በማሶጣት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ ም ካራማራ ተራራ ላይ ሰንደቅ አላማ ተክሎ ያውለበለበበት ታሪካዊ ድል ነው፤የካራማራ ድል።
ድሉ አንደ አደዋ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ህብረትና አንድነት እንዲሁም የሀገር ፍቅር ጽናት የታየበት ህበረ ብሄራዊ ድል ስለመሆኑ ታሪክ ይመሰክራል።