የሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲን ለመከለስ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲን ለመከለስ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ( ኢዜአ) የሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲን ለመከለስ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሶስት ትውልዶች ሴት አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በውይይቱ በየትውልዱ ሴቶችን ሲያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮች የተነሱ ሲሆን በየጊዜው የታዩ መሻሻሎችና በቀጣይ ያሉ ዕድሎችም ተቃኝተዋል።
በኢትዮጵያ በመጀመሪያው ትውልድ በሴቶች የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ብሶት ተኮር እንደነበሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በተለይም የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ገብተው መስራት ሲጀምሩ እንቅቃሴው ተጨባጭ ለውጦች ማምጣት መጀመራቸው ነው የተነሳው።
የመካከለኛው ትውልድ ላይ ሴቶችን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች መሻሻል ማሳየታቸውና አሁን ያለው ትውልድም የራሱ ጥያቄ ይዞ መምጣቱ ነው በውይይት መድረኩ የተነገረው።
ይሁንና ሶስቱም ትውልዶች ላይ የሚነሳ ነገር ግን መፍትሄ ያላገኘ ተግዳሮት መኖራቸውን የመካከለኛውና የአሁኑ ትውልድ ተወካዮች ይናገራሉ።
ዶክተር ስህን የመካከለኛው ትውልድ ተወካይ ቀደም ሲል የሴቶች ትምህርት ላይ የነበረው የተደራሽነትና ፍትሃዊነት ችግሮች በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ መሻሻሎች መኖሩን ተናግረዋል።
የአሁን ትውልድ ተወካይ ሴት በበከሏ በትዳር ውስጥ በእኩልነት የሚያምኑ ወንዶችን ማብቃት ካልተቻለ አንዲት ሴት የተማረች ብትሆንም በትዳሯ የምትጨቆን ከሆነ ውጤታማ ልትሆን አትችልም ብላለች።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ ሴቶች መብታቸውን ለማስከበር ያደረጓቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም ብለዋል።
የሴቶች ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ የሴቶች አደረጃጀቶችን በመፍጠር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች አሁን እየታየ ያለው የሴቶች ተሳትፎ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ተግባራዊ ከተደረገ ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲ መከለስ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን ፖሊሲው የሴቶችን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች እንዳሉበት ነው የገለጹት።
ለዚህ ደግሞ ሚኒስቴሩ ፖሊሲውን ማሻሻል የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ፖሊሲው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልና የስራ ዘርፎች የሚያሳትፍ ሲሆን ሚኒስቴሩ በአሁን ጊዜ የፖሊሲው መከለስ አስፈላጊነት ላይ የዳሰሳ ጥናት እያደረገ ነው ብለዋል።
የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ የተያዙ ዕቅዶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ሚኒስትሯ።
በኢትዮጵያ የሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ ከተደረገ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
የመጋቢት ወር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በዘመቻ መልኩ የሚከናወኑ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።