የካራማራ ድል የኢትዮጵያ ጦር በዜያድባሬ ጦር ላይ ታሪካዊ ገድል የፈጸመበት ነው ... በውጊያው የነበሩ የጦር መኮንኖች

3217

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2013(ኢዜአ) የካራማራ ጦርነት ድል የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ የወራሪው የዜያድባሬ ጦር ላይ ታሪካዊ ገድል የፈጸመበት ነው ሲሉ በአውደ ውጊያው ላይ የነበሩ የጦር መኮንኖች ገለጹ።

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነት ሁልጊዜ ዘብ መቆም አለባቸው ብለዋል።

 የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል መታሰቢያ ዛሬ በአዲስ አበባ ኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ ተከብሯል።

ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ዚያድባሬ 'ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት' በሚል "ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል" እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው የሚታወስ ነው። 

ይሄን እውን ለማድረግ በ1969 ግልጽ ወረራ ኢትዮጵያ ላይ ፈጸሙ።

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኩባ ወታደሮችም የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድል በማድረጉ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በአደባባይ ታወጀ።

በካራማራ ጦርነት በአውደ ውጊያው ላይ የነበሩ የቀድሞ የሠራዊት አባላት ብርጋዴል ጀኔራል ሃይለመለኮት ማሞ፣ ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና እና መቶ አለቃ በቀለ በላይ ድሉን አስመልክቶ የምስክርነት ቃላቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

ጦርነቱ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የገባውን ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ከአገር ለማስወጣትና ድል ለማድረግ የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑንና ኢትዮጵያም በድሉ ክብሯ መጠበቁን ገልጸዋል።

በምድርና በአየር ወራሪ የሶማሊያ ጦርን በመደምሰስ የኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪካዊ፣ አስደናቂ ገድልና ጀብድ መፈጸሙንም ተናግረዋል።

በወቅቱ የነበሩ የሠራዊቱ አባላት ሕይወቴ ከአገሬ አይበልጥም ብለው ያሳዩት ተጋድሎ የማይረሳ ነው ብለዋል የጦር መኮንኖቹ።

ኢትዮጵያዊያን ሁልግዜ አገራቸውን ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸውና ለሉዓላዊነቷ ዘብ መቆም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ የካራማራው ጦርነት ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ኃይል ላይ ያስመዘገበችው ድል መሆኑን ገልጸዋል።

በጦርነቱ ላይ የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን በመሆን መዋጋታቸውንና 163 ኩባዊያን ወታደሮች የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።

"የተገኘው ድል በኢትዮጵያና በኩባ ሕዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር የሚያሳይ ምስክር ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያና ኩባን ከ43 ዓመት በፊት ያስተሳሰረ የወዳጅነትና ትብብር መንፈስ አሁንም አለ" ያሉት አምባሳደር ቪልማ፤ አገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማጠናከር እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የደቡብ አሜሪካና ካሪቢያን አገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ቤኩማ መርዳሳ ፣ "የካራማራ ድል ኢትዮጵያዊያን የዚያድ ባሬ ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ወረራ በመመከት ድል የተጎናጸፉበት ታሪክ ነው" ብለዋል።

ድሉ ኢትዮጵያ ወራሪ ሃይልን በማሸነፍ ዳግም ነጻነቷን ያወጀችበትና ኢትዮጵያዊያን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ሉዓላዊነታቸውን ያስጠበቁበት እንደሆነም አክለዋል።

ኩባ በጦርነቱ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ያሳየችው አጋርነት ኢትዮጵያ ሁሉጊዜ የምታወሳውና የምትዘክረው እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበበ አያሌው ማህበሩ በአጥንትና በደም የተሳሰረውን የኢትዮጵያና ኩባ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ ኩባ ከኢትዮጵያ ጎን ሆና ላሳየችው አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ታማኝ በየነ "የካራማራ ድል ኢትዮጵያዊያን ደማቸውን በማፍሰስና አጥንታቸውን በመከስከስ ኢትዮጵያን ያቆዩበት ታሪካዊ ገድል ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በታሪክ ከተገኙ ድሎች በመማር አሁንም ቢሆን ከልዩነታቸው ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም አገራቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁልጊዜም ታሪክ ለሰሩ ወታደሮችና የጦር ሠራዊት አባላት ክብር መስጠት አለባቸው ብለዋል።

በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ በተከበረው የድል በዓል የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በጦርነቱ ለተሰው ጀግኖች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ከኢትዮጵያዊያን የየካቲት ወራት ድሎች አንዱ የሆነው የካራማራ ድል 43ኛ ዓመቱን አስቆጥሮ የድል በዓሉ በኢትዮጵያዊያን ዛሬም እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም