ቀጥታ፡

ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2013 ዓ.ም (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የድርጅቱን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ ሃና አርአያስላሴ መግለጫ ሰጥተዋል።

ወይዘሮ ሃና እንዳሉት፣ ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከአራት ሚሊዮን በላይ የፖስታ ትራፊክ አንቀሳቅሷል።

በዚህም ከ90 በመቶ በላይ እቅዱን ማሳካቱን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ 233 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።

ገቢው የተገኘው ከደብዳቤ፣ ጥቅልና ኢ ኤም ኤስ አገልግሎቶች ሲሆን የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የቤት ለቤት የፖስታ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም የተገኘበት እንደሆነም የተናገሩት።

እንደ ወይዘሮ ሃና ገለጻ ባለፈው ዓመት ድርጅቱ ገጥሞት በነበረው ብልሹ አሰራር ሳቢያ የበጀት መዝጊያው ላይ 34 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ገጥሞት እንደነበረው አስታውሰው አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ።

ከእርምጃዎቹ ውስጥ ቁጥጥሩ የጠበቀ ማድረግ አንዱ መሆኑን ያብራሩት ሥራ አስፈጻሚዋ የፋይናንስ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ከየቅርጫፎቹ የሚሰበሰበው ገቢ ወደ ማዕከል ፈሰስ እንዲደረግ ማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ድርጅቱ እስከ 10 ዓመት ድረስ የቆየ እዳዎች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው በተለይም የግብር እዳ ሙሉ በሙሉ ተከፍሏል ብለዋል።

ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል ዓለም አቀፉ የሂሳብ አያያዝ አይ ኤፍ አር ኤስ አሰራርን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎትም ፈጣን ለማድረግ ተገቢውን የሰው ኃይል ያሟላ ዲፓርትመንት እንዲቋቋም የተደረገ መሆኑን ገልጸው የደንበኞች ቅሬታ አፈታትና ካሳ ክፍያ ላይም ያለውን ችግር የማስተካከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የመልዕክት ደህንነት ላይ ከበፊቱ የተሻለ ነገር ቢኖርም የሚጠበቀው ያህል አይደለም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከመልዕክት መጥፋት ጋር በተያያዘ ድርጅቱ 200 ሺህ ብር ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታውቀዋል።

ድርጅቱ ገቢውን ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችም የጀመረ ሲሆን ጡረታና ክፍያ፣ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች የውክልና ክፍያ በመፈጸም ገቢ እየሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ሌላው የጀመረው አዲስ አገልግሎት ደግሞ የአሜሪካ ቪዛ አመልካቾችን ፓስፖርት የማደስ ስራ አንዱ መሆኑን ገልጸው አገልግሎቱን በአዲስ አበባ፣በባህርዳርና በሀዋሳ ለሚገኙ ደንበኞች እየሰጠ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 900 ቅርንጫፎች ያሉት መሆኑን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም