ቀጥታ፡

በጎ -ፈቃደኛ ወጣቶች በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ በነጻ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገለጹ

አሶሳ ፤ የካቲት 26 / 2013(ኢዜአ)  በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ተገኝተው ህብረተሰቡን በነጻ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የሀገር አቀፍ በጎ- ፈቃደኞች ሠልጣኝ ወጣቶች ገለጹ፡፡

ከአምስት ክልሎች ተውጣጥተው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለ45 ቀናት የበጎ ፈቃድ አሰጣጥ ስልጠና  የተከታተሉ  350 ወጣቶች ስልጠናቸውን አጠናቀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል  ወጣት ሠላም ቢሻን  ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በቆይታዋ በዩኒቨርሲቲ ለሶስት ዓመት ከቀሰመችው  እውቀት በላይ ትምህርት ማግኘቷን ተናግራለች።

በዚህም   የሀገር ፍቅር አንዱ እንደሆነ የጠቀሰችው ወጣቷ ይህም ምሉዕ እንድሆን አድርጎኛል ብላለች፡፡

በቀጣይ በማንኛውን ቦታ  ተሰማርታ ሀገሯንና ህዝቧን  በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ዝግጁ  መሆኗን ገልጻለች፡፡

ወጣት ደሚቱ ተመስገን በበኩሏ ስልጠናው ከአምስት ክልሎች ከመጡ ወንድሞቼ ጋር የባህል ትውውቅ በማድረግ ማህበራዊ አንድነቴን በማጠናከር በራስ መተማንን አሳድጎልኛል ትላለች፡፡

ሌሎች ወጣችም ይህን እድል ቢያኙ ሀገር ትለወጣለች ስትልም ተናግራለች፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም በድህነት የምትጠራበትን የተሳሳተ ገጽታ መቀየር አለበት ያለው ደግሞ  ወጣት ወጣሳ  ካሳ ነው፡፡

ይህን የተሳሳተ ገጽታ ማስተካካል የሚያስችል አቅም አለን ያለው ወጣቱ ይህም ሃገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት፣ ቱባ ባህሎች፣ እና የተማረ የሰው ሃይል ጠቅሷል፡፡

በበጎ ፈቃድ የሃገሩን ገጽታ ለመገንባት በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህም ከምንም በላይ የህሊና እርካታ እንደሚሰጠው ወጣቱ  ገልጿል፡፡

ሃገር እንድትለወጥ ወጣቱ አስተሳሰቡ መቀየር ያለበት አሁን ነው ያለው ሌላው ወጣት ዮሐንስ አደላ  በ45 ቀናት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በተግባር ለመቀየር እንደሚጥር ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያዊነትን  መሠረት በማድረግ በሃገሪቱ የትም ቢላክ ያለአድለዎ በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ተዘጋጅቼያለሁ፤ በጎ ስራዬን የማከናውነው ደግሞ ሰው የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በመያዝ ብቻ ነው ብሏል፡፡

በሠላም ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ መከላከል ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ እና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠው ስልጠና አስተባባሪ አቶ ይብዛ መንገሻ በመጀመሪያው የ45 ቀናት ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ስልጠና በ19 ዩኒቨርሲቲዎች መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡

ዘጠኝ ሺህ ያህል ወጣቶች የተሳተፉበት ይኸው ስልጠና በአብዛኞቹ የኒቨርሲቲዎች እየተጠናቀቀ መሆኑንና  በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በይፋ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡

ወጣቶቹ በቀጣይ አስር  ወራት በተለያዩ በጎ ፈቃድ ስራ እንደሚሠማሩ ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ ስራቸውን አጠናቀው ሲመለሱ መንግስት በተመረቁባቸው የትምህርት ዘርፎች እንዲሠማሩ ከወዲሁ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ ይብዛ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም