በመተከል ዞን ወደ ጫካ የገቡ የጉምዝ ማሕበረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን ወደ ጫካ የገቡ የጉምዝ ማሕበረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸው ተገለጸ
የካቲት 26/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ከሶስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች እና በእነርሱ አማካኝነት ጫካ ገብተው የነበሩ ከ68 ሺህ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲከታተል የተቋቋመ ኮሚቴ ገለጸ።
ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ኮሚቴ በዞኑ ያለውን ሁኔታ መጎብኘቱ ተገልጿል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሀሙ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚቴው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
በዞኑ ተከስቶ በነበረው ግጭትም የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ሰብዓዊ ቀውስ ማጋጠሙንና ንብረት መውደሙን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙና ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉም ሕዝብ ባወያዩበት ወቅት ገልጸዋል።
"በዞኑ በኢንቨስትመንት ስም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የወሰዱ ግለሰቦች የጉምዝ ወጣቶችን በማሰልጠን ለእኩይ ተልዕኮ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል" በማለት ነው የተናገሩት።
በዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እያሰፈነ መሆኑን ኮሚቴው መታዘቡን ገልጸዋል።
ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ወደ ጫካ ገብተው ሸፍተው የነበሩ የጉምዝ ታጣቂዎችም መንግስት ያደረገውን የማግባባትና የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን ነው አቶ አብዱላሂ የገለጹት።
በዚህም ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ታጣቂዎችና በታጣቂዎቹ አነሳሽነት ወደ ጫካ ገብተው የነበሩ 68 ሺህ ገደማ የጉምዝ ማሕበረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት መግባታቸውን ኮሚቴው ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የሚሊሻ፣ መደበኛ ፖሊስና ልዩ ኃይል ስልጠና እንዲሁም የየአካባቢ ነዋሪዎችን መሰረት ያደረገ የአመራር ሽግሽግ መደረጉንም ነው ያብራሩት።
የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ በዚህ ወቅት በዞኑ አዲስ ቀውስ፣ ሞትና መፈናቀል ለማቆም መቻሉንም ከግብረ ኃይሉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
"ኮሚቴው በዞኑ ከ125 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎችና በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኙ ተረድቷል" ብለዋል።
ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ አንጻር የተሟላ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑንና ይህም መስተካከል እንዳለበት ኮሚቴው አሳስቧል።
አቶ አብዱላሂ በተጨማሪም "በየትኛውም መልኩ ይሁን በወንጀል ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦች ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ መሆን አለባቸውም " ብለዋል።
አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ሂደት ሕዝቡ ጥቆማ ማድረስ የሚችልበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ጠቁመው፣ "መንግስትም የተለያዩ መረጃዎችን ተጠቅሞ የሕግ የበላይነት ያስከብር" ሲሉ አሳስበዋል።