ባህሪያተ ብዙ ገዳይ

48

መንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረቅ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም በዓለማችን ትልቅ ስጋትን እንደደቀነ ነው። መነሻውን በቻይና ውሃን ግዛት ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መላውን ዓለም አዳርሶ አሁን ላይ በተለያዩ አዳዲስ ዝርያዎች እየተከሰተ ስለመሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በስፔን የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል።

በእንግሊዝ በስፋት በሚታየውና B.1.1.7, የሚል ስያሜ በተሰጠው ዝርያ ከአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአዲሱ ዝርያ የተያዙ እንደሆነ የጥናት ውጤቶች ያስረዳሉ፡፡ በእንግሊዝ እና ስፔን 80 በመቶ፣ በአየርላንድ 60 በመቶ እንዲሁም በስውዘርላንድና በፈረንሳይ እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት በአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተያዙ መሆናቸውን በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች አመላክተዋል፡፡ 

በደቡብ አፍሪካ በታህሳስ ወር የተገኘውና አሁን ላይ በብራዚል፣ በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ከተማ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ያለው አዲሱ ዝርያ B.1.351 የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ዝርያው ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ቀደም ሲል በሌላ የቫይረሱ ዝርያ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችን በድጋሚ እንዲያዙ የማድረግ አቅም ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ ክትባትን በቀላሉ የሚላመድና ታማሚዎችን ለተጨማሪ ህመም የሚዳርግ ሆኖ መገኘቱ እንደሆነ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡

አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ካላቸው አስቸጋሪ ባህሪያት መካከል ለህክምና ክትትል እና ለመከላከል የሚሰጡ መድሃኒቶችን በመላመድ የሚያጠቁ ሆነው መገኘታቸው መሆኑ ይገለጻል። ለምሳሌ በB.1.351 ዝርያ የተያዙ ሰዎች የአስትራዜኔካ ክትባት ሲሰጣቸው ለተጨማሪ ህመም የተዳረጉት ቫይረሱ ክትባቱን በመላመዱ እና ወደ ማጥቃት ደረጃ በመሸጋገሩ ምክንያት እንደሆነ የኔዘርላን እና የስፔን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

ተመራማሪዎቹ B.1.1.7 ብለው የሰየሙት አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በባህሪው ፕሮቲኑን በውስጡ ባሉት ስብስቦች ያስበላና በቫይረሱ የላይኛው ክፍል ላይ እንዲለጠፍ ያደርጋል ከዛም በፕሮቲኑ አማካኝነት ቫይረሱ በአፍንጫና በጉሮሮ እና በሌሎች የሰዎች አካላት ሴሎች ላይ ተለጥፎ እንዲቆይ ዕድል እንደሚሰጠው እንደሚያደርገውም ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ነው ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል አፍንና አፍንጫን ባልታጠበ እጅ ከማሸት መቆጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም፣ እጅን ቶሎ ቶሎ በሳሙና መታጠብ ወይም ሳኒታይዘር መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ የሚመከረው፡፡  በነባሩም ሆነ በአዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ደረቅ ሳል፣ በደረት አካባቢ ምቾት ማጣት፣ የትንፋሽ ማጠርና ኦክስጅን የመሳብ ችግር በምልክትነት እንደሚያሳዩ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡ 

በተለያዩ ሀገራት ለአዲሱ የኮረሮና ቫይረስ ዝርያ በፍጥነት መሰራጨት ምክንያት የሆነው ዜጎች ቤት እንዲቀመጡ የተጣለውን መመሪያ በመጣስ፣ የአፍና አፍጫ መሸፈኛ ጭምብል አለመጠቀም፣ ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን በመዘንጋት፣ ከመጠን ያለፈ ቸልተኝነት በማሳየት፣ በዓላትን ለማክበር መሰባሰባቸውና የመሳሰሉት መሆኑን በስፋት ይነገራል። የኮሮና ቫይረስ አዳዲስ ዝርያዎች በባህሪያቸው ልክ እንግሊዝ ውስጥ እንደታየው አይነት ከፍተኛ ህመም ከሚያስከትሉ የተለያዩ በሽታዎች ጋር በመጣመር ቫይረሱ በቀላሉ እና በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው በወረርሽኝ መልክ እንዲተላለፍ በማድረግ ለጽኑ ህመም ከፍ ሲልም ለሞት ይዳርጋሉ፡፡

የቫይረሱ ተለዋዋጭ ባህሪና በየጊዜው የሚገኙ አዳዲስ ዝርያዎች ክትባቱን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ እንዳደረገባቸው ተመራማሪዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ ዘጠኝ አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም ሀገራት ተረጋግተው አንድ ወጥ የሆነ የመከላከያ ዘዴ ወይም ክትባት ተግባራዊ ለማድረግና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አዳጋች እንዳደረገው የህክምና ጠበብቶች ይናገራሉ። የቫይረሱን አደገኛነት በቀላሉ ለመገንዘብ እጅግ ጠንካራ እና ዘመናዊ የጤና መሰረተ-ልማት ባለቤት የሆኑ አሜሪካና ሌሎች የበለጸጉ ሀገራት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ማየት በቂ ነው፡፡

የአፍሪካ በሽታ መከላከልልና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) መረጃ እንደሚያመላክተው በአፍሪካ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዙም ሆነ ህይወታቸውን እያጡ ያሉት ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመሄዱም ባሻገር በቫይረሱ እየተያዙ ያሉት ሰዎች ዕድሜ  ከ30 እስከ 39 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይህም አህጉሪቱ ምን ያህል አምራች የሚባለውን የሰው ሀብቷን በዚህ ወረርሽኝ እያጣች እንደሆነ የሚያመለክት ነው።

የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከሁለት ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከ160 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ታላላቅ የሀገር ባለውለታዎችን እና ምሁራንን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የቫይረሱ ስርጭት አሁንም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። በተለይ የጽኑ ህሙማን ቁጥር ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ እያለ መጥቷል።

ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሕክምና ክትትል ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 የሚሆኑት ጽኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥም ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ የሚጠቀሙ ናቸው።  የጽኑ ሕክምና ክፍል ከገቡት ውስጥ ደግሞ 59 በመቶ ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈም መረጃው ያመለክታል።

አሁን ላይ ለሚስተዋለው ችግር እንደ ዋነኛ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ቸልተኝነትና መዘናጋት፤ በሽታው ጠፍቷል ወይም በሽታው በእኔና በቤተሰቤ ብሎም በማሕበረሰቤ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብሎ ካለመረዳት እና እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ሚና ባለመወጣቱ  ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

አሁን እየታየ ያለው ቸልተኝነት በተለይ ርቀትን ያለመጠበቅና አስገዳጅ የመከላከያ እርምጃዎችን ያለመተግበር በሀይማኖት ተቋማት፣ በትራንፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት ይታያል። የመንግስት አስፈጻሚ አካላት፣ የመንግስትም ሆነ የግል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመከላከያ ፕሮቶኮሎችን በቸልተኝነት ሲያልፉት እእየተስተዋለ ይገኛል። የሚዲያ ተቋማትም ቢሆን በተገቢው ደረጃ ግንዛቤ የመፍጠርና የማንቃት ስራውን ዘንግቷል ማለት ይቻላል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ማብራሪያ "ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያሳዩት ቸልተኝነት አሳሳቢ ነው" ሲሉ ገልጸዋል። ሚኒስትሯ እንደገለጹት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ዓርአያ መሆን የነበረባቸው አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ቸልተኛ መሆናቸውን በየመድረኩ መመልከት ተችሏል። እነዚህ ለኅብረተሰቡ ዓርአያ ይሆናሉ የተባሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስና ህጎች ሲጣሱም ቆሞ የመመልከት ቸልታ እንደታየባቸው ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በቅርቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራም ላይ የነበረው ቸልተኝነት ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ መገመት አያዳግትም። የመንግስት አካላትም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ትላልቅ መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ያለምንም ጥንቃቄ ሲሰበሰቡ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ቀጥሎ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደመሆኑ ስብሰባዎች በብዛት እንደሚካሄዱ ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ እንደ ሀገር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ስነልቦናዊ  ጉዳዮች ዙሪያ ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በባህሪው የተወሰኑ አካላት በሚያደርጉት ጥንቃቄ ብቻ መከላከል የማይቻል በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የመላ ህዝቡን ንቃተ ህሊና ማደግና ንቁ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልጋል፡፡ አንዱ የመንግስት አካል አዘጋጅቶ እና አጽድቆ ወደ ሌላው ባስተላለፈው የህግ ማዕቀፍ ብቻ ወረርሽኙን መከላከል በፍጹም አይቻልም፡፡ መፈጸምና ማስፈጸምን የግድ ይላል፡፡

የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ከነባሩም ሆነ ከአዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ራስን ለመጠበቅ ቀደም ሲል ሲሰራ የነበረውን የመከላከል ስልት በአግባቡ እና በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ አዋጭ ነው፡፡ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ ማለት በርካታ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲፈጠሩ ዕድል መስጠት በመሆኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ባለበት ለመግታት የመከላከያ ስልቶችን በሙሉ ሳይታክቱ ተግባራዊ ማድረግ ብቻ በቂ መሆኑን ይመክራሉ፡፡ ስለሆነም በየጊዜው ባህሪዩን እየቀያየረ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ሀገር  እያደረሰ ያለው እና ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የመከላከል ስራ ለአፍታም ቢሆን ጊዜ የማይሰጠው በመሆኑ ከግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው የሚመለከተው ሁሉ  በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል መልእክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም