"ከጓዳ እስከ ጦር ሜዳ" - ኢዜአ አማርኛ
"ከጓዳ እስከ ጦር ሜዳ"
በገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)
እንደአለመታደል ሆኖ ለበርካታ ምእተ አመታት በዓለማችን በተካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊዎች ተደርገው የሚወሰዱት ወንዶች ስለመሆናቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በአሸናፊነትም ሆነ በተሸናፊነት በመጠቀስ ረገድም አብዛኛውን ቦታ ወንዶች እንደያዙት ይነገራል። ይሁን እንጂ ሴቶች በየዘመናቱ ጦር እስከ መምራት የዘለቀ ጀግንነት ያለው ታሪክ ማስመዝገባቸውን የሚያወሱ በርካታ ሰነዶች አሉ።
ከዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አኳያ ሲታይ የተለያዩ ሀገራት ባደረጓቸው ጦርነቶች ውስጥ ሴቶች በሁሉም ሂደቶች ተጋድሎ በማድረግ ረገድ ከወንዶቹ የሚስተካካል ድርሻ እንደነበራቸው ማሳያዎች አሉ። ለአብነት የጥቁር አሜሪካዊቷ ሃሪየት ታብማን፣ እንግሊዛዊቷ ጆን ኦፍ አርክ በብዛት የተነገራላቸው ሲሆን የሴልቲኳ ንግስት ባውዲካ እና ግብጻዊቷ ክሊዮፓትራ ይጠቀሳሉ። በአፍሪካም አንጎላዊቷ ንግስት ንዚንጋ ምባንዲ፣ ናይጄሪያዊቷ ንግስት አሚና እንዲሁም ጋናዊቷ ንግስት ያአ አሳንቴዋ የቅኝ ግዛት መስፋፋትን አንቀበልም በማለት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለነጻነት መፋለማቸውን ታሪክ ያስታውሰናል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀስላቸው ሴቶች መካከል ንግስተ ሳባ፣ ንግስት እሌኒ፣ ወሎን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ንግስት ወርቂቱ፣ ንግስት ዮዲት፣ ንግስት ሰብለወንጌል፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ ቃቂ ወርድዎት፣ ንግስት ፉራ እንዲሁም እቴጌ ጣይቱ የጀግንነት ታሪክ ካስመዘገቡ ሴቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ለዚህም ነው "ወግጅልኝ ዜማ ወግጅልኝ ቅኔ፤ ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ" የሚል ቅኔ የተቀኘላቸው።
የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ጥቁር አፍሪካውያን ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃ እንዲወጡ በር የከፈተ ወሳኝ ድል ነው። ይህም በመሆኑ አድዋ በመላው አፍሪካውያን ዘንድ የጋራ ትውስታን የፈጠረና ትልቅ ስፍራም የያዘ ክስተት ተደርጎ ይወሰዳል። የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን የአንድነት፣ የፍቅርና የወዳጅነት መንፈስ ጎልቶ እንዲታወቅ ያደረገና ለትውልድ የሚሸጋገር ታላቅ ገድል ነው። በዚህ ጦርነት መላው ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ሆነዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል።
የአድዋ ጦርነት ጾታ አልተለየበትም። ወንዶች ብቻ ተዋግተው ያሸነፉበት ጦርነት ሳይሆን ከሀገሪቱ ከሁሉም አካባቢዎች የተሰባሰቡ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ሴቶች ተሳትፈውበታል። የሴቶች አስተዋጽኦ ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ በአዋጊነትና በተዋጊነት እንዲሁም በቅስቀሳውም ዘርፍ ስለነበር የአብዛኛዎቹ ተግባር ድርብ ነበር ማለት ይቻላል። በወቅቱ ከነበሩት ስመጥር አርበኞች መካከል ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን፣ ወ/ሮ አለሚቱ መኮንን እና ወ/ሮ ዘነበች ወ/የስ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር በሚለው መጽሃፉ ወደ አድዋ ለዘመተው ግዙፍ ጦርና ለአዝማች መኳንንቱና መሳፍንቱ በቀን ሶስት ጊዜ ትኩስ ምግብ አብስሎ ማቅረብ፣ ለወታደሩ ውሃ ጠላና ጠጅ ማዘጋጀት፣ ለሚቀጥለው ቀን የሚያስፈልግ እህል መፍጨትና ማቡካት፣ የቆሰሉ ወታደሮችን መንከባከብ በሴቶች ጫንቃ ላይ ያረፈ የየእለት ተግባር እንደነበር ገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር አባል ወይዘሮ ማሚቴ ምህረቱ “ሴቶች ከአድዋ ድል በስተጀርባ ግንባር ቀደም ኃይል ነበሩ፣ ምግብና ውሃ ሲያዘጋጁ ነበር፤ ለቆሰሉት የህክምና አገልግሎት በመስጠት፣ በስነልቦና በማበረታታት ሲሳተፉ ነበር” ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ “ነፃነት ወይም ሞት” የሚል መፈክር በመያዝ በወኔ ትግል ያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል።
መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለክብራቸው ለነጻነታቸውና ለሉአላዊነታቸው የጾታ፣ የብሔር የሃይማኖት እና የሃብት ደረጃ ልዩነት ሳይበግራቸው በተሰዉበት የዓድዋ ጦርነት አውደ ውጊያ በወቅቱ ከነበሩት የጦር መሪዎች መካከል ቀድሞ ስማቸው የሚነሳው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው። እትጌ ጣይቱ በአድዋ ጦርነት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ በህግና ዳኝነት፣ በውጭ ግንኙነት፣ ብሎም የዝመናና የሥልጣኔ ጥረቶች ውስጥ የነበራቸው አበርክቶ ጉልህ ነበር።
እቴጌይቱ ከአድዋ ጦርነት በፊት በነበረው የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17 ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመግዛት የሸረቡትን ሴራ እንዲመክን አድርገዋል። የውጫሌው ስምምነት 17ኛው አንቀጽ ላይ በጣልያንኛ ትርጉም መሰረት ኢትዮጵያ በጣልያን ሞግዚትነት እንድትተዳደር የወጠኑት መሆኑን የተገነዘቡት እቴጌዋ ሁኔታውን ለንጉሱ አስረድተው ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንዳትቀበለው ማስደረግ ችለዋል። ይህን ተከትሎ በሃገራቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለጦርነቱ መነሻ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ እቴጌይቱ የውጫሌው ስምምነት በማፍረስ የቅኝ አገዛዝ ስልትን ያከሸፉ ጀግና ሴት በመሆናቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በአድዋ ጦርነት ወቅት እቴጌይቱ በብልሃት የሚመሩት ሠራዊት እንዳየሱስ በተባለው አካባቢ ባለ ኮረብታ ላይ በመመሸግ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችል የነበረው የጣሊያን ጦር እየተጠቀመበት የነበረውን የምንጭ ውኃ ጉድጓድ ኢትዮጵያውያን እንዲይዙት በማድረግ ምሽግ ውስጥ የነበሩት የጣሊያን ወታደሮች ያለውሃ እንዳስቀሯቸውና ይህም ለጣሊያን ጦር ሽንፈት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው የታሪክ ልሳናት ያስረዳሉ። በተሰለፉበት አውደ ውጊያ ከራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ከራስ መኮንን፣ ከፊታውራሪ ገበየሁ ከራስ አሉላ፣ ከደጃች ባልቻ ሳፎ፣ ከራስ አባተ ባልተናነሰ ሁኔታ አኩሪ ድሎችን ስለማግኘታቸው በርካታ ጽሑፎች ያመለክታሉ።
አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ለውጥ ፈርቀዳጅ ስለሆኑ ሰዎች (Pioneers of change in Ethiopia) በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ እንዳብራሩት እቴጌ ጣይቱ አዲስ አበባ ከተማን እንድትመሰረት ከማድረግ ጀምረው ስልጣኔ ሊያመጡ ይችላሉ የሚሏቸውን ሃሳቦች ለንጉሱ አፄ ሚኒሊክ አቅርበው በማስወሰን አለፍ ሲልም ራሳቸው በማስፈጸም ረገድ ድርሻቸው ጉልህ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ወራሪው የጣሊያን ሰራዊት አድዋ ላይ ከተሸነፈ በኋላ አርባ አመታት ያህል ከባድ ዝግጅት አድርጎ ተመልሶ በመምጣት ኢትዮጵያን ለማስተዳዳር ያደረገው ሙከራ እንዳይሳካ፤ እንቅስቃሴዎቹም በከተሞች አካባቢ ብቻ እንዲወሰን ካስቻሉት አርበኞች ውስጥ በርካታ ሴቶች ነበሩ። በወቅቱ የነበሩት ሴቶች ሃገራቸውን ለመጠበቅ በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ በብዛት ተካተው ጦር አውደ ውጊያ ላይ ፊት ለፊት መሳተፍ ያልቻሉት ለተዋጊዎች የስነልቦና ድጋፍ በመስጠት ቶሎ የማይበላሹ ምግቦችን በማዘጋጀት ለጣሊያን ወታደሮች የተሳሳተ መረጃ በማቀበል እንዲሁም መንገድ በመዝጋት የታመሙ ወታደሮችን በባህላዊ መድሃኒቶች በመጠቀም የመንክባከብ ድርሻን የራሳቸው አድርገው በስኬት ተወጥተዋል።
ከአድዋ ድል የጀግንነት መንፈስ የተረከበው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በህወሃት ጁንታ ቡድን ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት የማይታመኑ አኩሪ የውጊያ ጀብዶችን በመፈጸም ረገድ የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ የህወሃት ጁንታ “መብረቃዊ ጥቃት” ያለውን እርምጃ በመከላከያ ሰራዊቱ አባላትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ የጦሩ ሰራተኞች ላይ ባደረሰበት ወቅት የሰራችው ጀብድ ታሪክ አይረሳውም። የጁንታው ቡድን “የሰሜን እዝን ከተቻለ መቆጣጠር ካልሆነም ከጥቅም ውጭ ማድረግ” የሚል ስውር ምክር በመያዝ በተጠና መንገድ በምሽት በመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጽሟል። በወቅቱ 20ኛ ክፍለ ጦር ሲመራ ለነበረው የጁንታው አዛዥ የግል አጃቢ የነበረችው ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ለተፈጸመው የሀገር ክህደት አጸፋ ለመመለስ እስከ ህይወት መስዋእት ድረስ ዝግጁ ሆነች።
ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ በወቅቱ የምታጅበው አዛዥ የጥፋቱ ዋነኛ ተዋናይ ስለመሆኑ በራሷ አንደበት ገልጻለች። "---ሁሉም ራሱን ለማዳን የሚያስችለውን አማራጭ እየተጠቀመ ሲሯሯጥ ሁኔታው ያስፈራው የከሃዲው ጁንታ ቡድን አዛዥ መፀዳጃ ቤት በመግባት ራሱን ለመደበቅ ሙከራ አደረገ” የምትለው ምክክትል አስር አለቃ ገበያነሽ “እኔ በትግራይ ሚሊሻና ልዩ ሃይል ጥይት ከምሞት አንተን ገድዬ ራሴን አጠፋለሁ” በማለት አዛዡን ከተሸሸገበት መጸዳጃ ቤት በማውጣት ሽጉጡን በመቀበል ማእረጉን በመግፈፍና ጫማውን በማስወለቅ በባዶ እግሩ በሌሊት እንዲጓዝ በማድረግ በጊዜያዊነት ኤርትራ ለሰፈረው የኢትዮጵያ ጦር አመራሮች እንዳስረከበችው ተናግራለች።
በየዘመናቱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሰላም፣ በልማትና ዴሞክራሲ እንዲያብብ በማድረግ ረገድ ያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። አሁንም ሴቶች በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በመሳተፍ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛል። ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊቷ ደራሲ መዓዛ መንግስቴ 'ዘ ሻዶው ኪንግ' በተባለው መፅሃፏ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለሃገራቸውና ለማህበረሰባቸው ነጻነት ያደረጉት አስተዋጽኦ የጥቂት ወንዶች ሚና በጎላበት የታሪክ አጻጻፍ የተሞላ መሆኑን አብራርታለች። ጸሐፊዋ ሴቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም የተጋድሎ ታሪክ አሁንም አልተነገረም በማለት ትሞግታለች። በርግጥም መነገር በሚገባው ደረጃ አልተነገረላቸውም። እናም የኢትዮጵያውያን ሴቶች ከጓዳ እስከ ጦር ሜዳ ብሎም በሁሉም መስኮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።