"የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃዎች የአገር ፍቅር የወለዳቸው የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ናቸው"... ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
"የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃዎች የአገር ፍቅር የወለዳቸው የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ናቸው"... ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2013(ኢዜአ) የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃዎች የአገር ፍቅር የወለዳቸው የኪነጥበብ ሥራዎች ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
"ቆሜ ልመርቅሽ" በሚል የተዘጋጀው የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ አልበም ትናንት ምሽት በወዳጅነት ፓርክ ተመርቋል።
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ከ400 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተ ሲሆን በሙዚቃ ሥራዎቹም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳችን አንስቷል።
ወደ 40 ከሚጠጉ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች በወሰዳቸው የሙዚቃ ሥራዎቹ ስለፍቅር፣ ስለአገር፣ ስለቤተሰብ፣ ስለፖለቲካ፣ ሥለተፈጥሮ ስለማኅበራዊ ጉዳዮች ተጫውቷል።
ከ15 ዓመታት በፊት ተጫውቷቸው ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ 10 ሙዚቃዎቹን ያካተተው “ቆሜ ልመርቅሽ” የሚለው አልበሙ በወዳጅነት ፓርክ በትናንትናው ዕለት ተመርቋል።
ቆሜ ልመርቅሽ የሙዚቃ አልበም ግጥሙ በያየህይራድ አላምረው፣ ዜማው በሞገስ ተካ እና ቅንብሩ በአበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ የተዘጋጀ ነው።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ “የጥላሁን የሙዚቃ ሥራዎች ገና በለጋ ዕድሜው በአገር ፍቅር ስሜት የቀረቡ የጥበብ ሥራዎች ናቸው” ብለዋል።
የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትና የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራም ጥላሁን ሰንደቅ ዓላማና የአገር ፍቅር ስሜት በልቡ እንዲሰርፅበት አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለዋል።
ኪነ-ጥበብና የኪነጥበብ ሰዎች ለአንድ አገር አዎንታዊ ተፅዕኖ አላቸው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በሥራዎቻቸው ማኅበረሰቡን ካነፁት መካከል ጥላሁን ገሠሠ ዋንኛው እንደሆነ ገልፀዋል።
“ለእውነት እሞታለሁ”፣ “ጩኸቴን ብትሰሙ” ሲል የተጫወታቸውን ሙዚቃዎች ላስተዋለም ኪነጥበብ ለተገፉትና ለተበደሉት የሰው ልጆች ነፃነት ጠያቂ መሆኗን ያሳያል ነው ያሉት።
በዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ በመሆንና ኅበረተሰቡን በአንድ በማስተሳሰር ሰዎች ስለአገራቸውና ስለመልክዓ ምድራቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ታላቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።
“ጥላሁን ያዜመላት፣ የናፈቃት እና የተመኛት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ ጠንክረን መስራት አለብን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ጥላሁን በሰራው ሥራ ለማኅበረሰቡ ቋንቋና መስተዋት መሆን ችሏል ብለዋል።
ይህም ጥላሁን በኅብረተሰቡ ዘንድና በቀጣይ ትውልድ እንዲታወስ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በዝግጅቱ የተወለደበትን 80ኛ ዓመትና ያረፈበትን 12ተኛ ዓመት በማስመልከት የሙዚቃ ኮንሰርት ተካሂዷል።
በሙዚቃ ክንውኑም አምስት ባንዶችና የአገሪቷ ወጣትና አንጋፋ የሙዚቃ ሰዎች በጥላሁን ገሠሠ የተዜሙ ሙዚቃዎችን አቅርበዋል።