የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2013(ኢዜአ) የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል በአዲስ አበባ ኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ ኃላፊዎች፣ በካራማራ ጦርነት የተሳተፉ የወቅቱ የሠራዊት አባላት እና ልጆቻቸው እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ሲያድ ባሬ 'ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት' በሚል "ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል" እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው የሚታወስ ነው።
የቅዠት ህልማቸውን እውን ለማድረግ በ1969 ግልጽ ወረራ ኢትዮጵያ ላይ ፈጸሙ።የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኩባ ወታደሮችም የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድል በማድረጉ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በአደባባይ ታወጀ።
ከኢትዮጵያዊያን የየካቲት ወራት ድሎች አንዱ የሆነው የካራማራ ድል 43ኛ ዓመቱን አስቆጥሮ የድል በዓሉ በኢትዮጵያዊያን ዛሬም እየተከበረ ነው።
በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ባለው የድል በዓል የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በጦርነቱ ለተሰው ጀግኖች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።