ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን መልሶ ሊቋቋም ነው

የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽንን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ገለፀ።

በትግራይ ክልል ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት አስመልከቶ ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

በትግራይ ክልል በነበረው ሕግን የማስከበር ሂደት ውስጥ በትግራይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸው ይታወሳል።

በዚህ ምክንያት ክለቦችና ስፖርተኞች የተበተኑ ሲሆን በክልሉ የሚደረጉ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ክንዋኔዎችም ተቋርጠዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትግራይን ወክለው ይሳተፉ የነበሩት ክለቦች ስሁል ሽሬ፣ ወልዋሎ አዲግራትና መቀሌ 70 እንደርታ በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ መሆን አልቻሉም።

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ የክልሉን ስፖርት ኮሚሽን ለማቋቋም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ያፈራቸው ሀብቶች ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች እና የስፖርት ትጥቆች በመውደማቸው የድጋፉ የመጀመሪያ ሥራ የክልሉን የስፖርት ኮሚሽን ቢሮ መቋቋም ነው ብለዋል።

ክልሉ በአትሌቲክስ ፣ በእግር ኳስ ፣ በብስክሌት እና በሌሎች ስፖርቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ውጤታማ ስፖርተኞች መፍለቂያ የነበረ ቢሆንም በተፈጠረው የሰላም ችግር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ቆሟል ነው ያሉት።

ከኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ሥር ከሚገኙ ሴክተር ማኅበራትና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆንም ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ለዚህም አስተባባሪና የቁሳቁስ ጉዳዮችን የሚያደራጅ ሁለት ኮሚቴ መቋቋሙንና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን እንደሚመራ አቶ ዱቤ ተናግረዋል።

የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽኖች፤ ታዋቂ አትሌቶች አሠልጣኞች እና የስፖርት ባለሙያዎችን በማነጋገርም ድጋፍ እንዲያደርጉ በማወያየት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በድጋፍ ማሰባሰቡም ሂደት የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

ሌሎችም የቁሳቁስ ድጋፎች እንዳሉና አጠቃላይ የሚደረገው ድጋፍ ወደፊት ይፋ እንደሚሆን አቶ ዱቤ ጠቁመዋል።

በመግለጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው ክልሉን በገንዘብም ይሁን በቁሳቁስ ክልሉን አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደረግ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም